የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ የ12ኛ ክፍል ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን እየተቀበለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ የ12ኛ ክፍል ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን እየተቀበለ ነው
ሚዛን አማን፤ ሐምሌ 6/2016(ኢዜአ)፦ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ የ12ኛ ክፍል ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን እየተቀበለ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በሁለተኛ ዙር ፈተና ከ3 ሺህ 50 በላይ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተናግድ የዩኒቨርሲቲው ጥናት፣ ምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ግርማ ጥላሁን(ዶ/ር) ለኢዜአ ተናግረዋል።
የሁለተኛ ዙር ተፈታኞች ቁጥር ከመጀመሪያው የማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች አኳያ በግማሽ ያህል አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተደረገው ዝግጅት መሠረት በስኬት ለማስተናገድ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የመጀመሪያ ዙር ፈተና በስኬት መጠናቀቁን አውስተው፤ ለዘርፉ የተሰጠው አገራዊ ትኩረት የተሻለ ትውልድን ለነገዋ ኢትዮጵያ ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ተገንዝቦ ዩኒቨርሲቲው ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አክለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ሰባት ሺህ የሚሆኑ የመጀመሪያ ዙር ተፈታኞችን ትላንት ማምሻውን እና ዛሬ ረፋድ ላይ ከሸኘ በኋላ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችን በመቀበል ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ተፈታኞች ፈተናውን ከመጀመራቸው በፊት በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን ማኖራቸውን አስታውቀዋል።