ቀጥታ፡

ማትሪክ ተፈታኟ የ10 ልጆች እናት 

                                                        ማትሪክ ተፈታኟ የ10 ልጆች እናት 

የ2016 ዓ.ም የ12ኛው ክፍል የመጀመሪያው ዙር የሆነው የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና በአገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከሐምሌ 3 ጀምሮ ለሶስት ቀናት መሰጠቱ ይታወሳል።

ከእነዚህም አሶሳ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ሲሆን፤ በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና ከወሰዱት መካከል  የ40 ዓመት ዕድሜ ያላቸው እናት ይገኙበታል።

እኚህ እናት ፈተናው በሚሰጥበት የመጨረሻው ቀን ከክፍሉ ጥግ ይዘው ፈተናውን መስመር በመስመር እያነበቡ መልሱን ያከባሉ። 

በትኩረት ለተመለከታቸው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ቆርጠው የተነሱ ይመስላሉ።  

እነሆ ተፈታኟ ከፈተና አዳራሽ ወጡ፤ መልካም ፍቃዳቸው ሆኖ ለቃለ ምልልስ ተቀመጥን። 

ወይዘሮ ኩመሌ ዳፋን ይባላሉ፤  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን የዛይ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፤  የ10 ልጆች እናት የሆኑት ተፈታኟ በልጅነታቸው ትዳር መመስረታቸውን አጫወቱኝ። 

ለልጆቼ አርአያ ለመሆን በማሰብ ያቋረጥኩትን የ12ኛ ክፍል ትምህርት ቀጥዬ ፈተና ለመውሰድ ወሰንኩ ሲሉ ገልጸውልኛል። 

አብረዋቸው ሲፈተኑ ከነበሩ የክፍሉ ተፈታኞች በበለጠ ተረጋግተው እና ጊዜያቸውን ተጠቅመው ፈተናውን ሰርተው እንደወጡ ነግረውናል። 

ወይዘሮ ኩመሌ "ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ውጤት ባመጣ ትምህርቴን ከመቀጠል የሚከለክለኝ አንድም ነገር የለም" ሲሉ ይናገራሉ። 

"ሃገራችንን የምንቀይረው ራሳችን በመማር እና ልጆቻችንንም በማስተማር ነው" ብለው እንደሚያምኑ እኚሁ እናት አስረድተዋል።

ከ10ሩ ልጆቻቸው መካከል የመጀመሪያዋ ልጃቸው በሚቀጥለው ሳምንት የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና እንደምትወስድ አመልክተው "ከልጄ ጋር በመፈተኔ በእጅጉ ደስተኛ ነኝ ብለዋል። 

የአሶሳ የኒቨርሲቲ ተወካይ ዶክተር መልካሙ ደሬሳ የ12ኛ ክፍል ተፈታኟ የ10 ልጆች እናት ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ተጉዘው  ወደ አሶሳ በመምጣት ፈተናውን መውሰዳቸው በአርአያነት የሚጠቀስ ሲሉ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው  4 ሺህ 200 የሚጠጉ ተማሪዎች  የሰጠው የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አስታውቀዋል። 

ሁለት ተማሪዎች ፈተና እየወሰዱ መውለዳቸውን ጠቅሰው፤  ህክምና አግኝተው ፈተናውን እንዲጨርሱ መደረጉን ተናግረዋል። 

ሌሎች 300 ያህል ተፈታኝ እናቶች ደግሞ የልጆቻቸው ሞግዚቶች በዩኒቨርሲቲው አልጋ ይዘው እንዲያግዟቸው በማድረግ ፈተናው እንዲወስዱ መደረጉን ዶክተር መልካሙ አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም