ቀጥታ፡

በኢሉባቦር ዞን የፍትህ አገልግሎትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አስደግፎ ተደራሽ  ለማድረግ  የተጀመረው ስራ ይጠናከራል- አቶ ናቶሊ ዓለማየሁ

መቱ፤ ሐምሌ 6/2016(ኢዜአ)፦ በኢሉባቦር ዞን የፍትህ አገልግሎትን ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ የሚጠናከር መሆኑን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ናቶሊ ዓለማየሁ ገለጹ።

በዞኑ የፍርድ ቤት ዳኞች ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ በመቱ ከተማ አካሂዷል።

አቶ ናቶሊ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በዞኑ የፍትህ አገልግሎትን በጥራት ተደራሽ ለማድረግ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መጠቀም ወሳኝነት አለው።

የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፈጣንና ጥራት ያለው የፍትህ አገልግሎትን ተደራሽነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ከፍተኛ ድርሻ ያለው ከመሆኑም በላይ፣ በሰው ኃይል እጥረት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማቃለል እገዛ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡ የዘመነ፣ ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለውና ተደራሽ ለማድረግ ደግሞ የመረጃ፣ የባለሙያ ስልጠናና የጥገና ማዕከላት የማቋቋም፣ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥን ማስፋፋት የጉባኤው ዋነኛ አጀንዳ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።


 

በዞኑ የፍትሕ ስርዓት ማሻሻያ ኮሚቴ ሰብሳቢና የኢሉባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በበኩላቸው በዞኑ የፍትሕ ተደራሽነትና ጥራትን ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎትን ማስፋፋት የተወዳዳሪነት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም በዞኑ ያለውን የፍትህ አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ስራዎች ላይ የፍትህና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ በመሆኑ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል።

በዞኑ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ለማሳካት የሚያግዙ የኔትወርክ ዝርጋታ፣ ግብዓቶች ማሟላት፣ የግንኙነት ሥርዓት ማዘመን ሥራዎች ሊተኮርባቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የፍትህ አገልግሎት ሥርዓት ተደራሽነትን ለማሳደግ ለባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ትኩረት እንዲሰጥ ዋና አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል።


 

አቶ ካሳሁን አሚድ የተባሉ የጉባዔው ተሳታፊ የፍትህ አገልግሎቱን ለማዘመንና ተደራሽነቱን ለማስፋት እየተደረገ ባለው ጥረት ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

የአገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ የቅንጅት፣ የገለልተኝነት፣ የነፃነት ጉዳዮች ዙሪያ ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላት የሁሉንም አካላት ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።

አቶ ዓለሙ ለገሰ የተባሉ ሌላው ተሳታፊ በበኩላቸው የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው እንዲሁም ተአማኒ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት አስተዋጽኦው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ያለው የዳኞች እጥረት ግን የፍትህ አገልግሎትን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ክፍተት ስለሚፈጠር  ሊታሰብበት ይገባዋል ብለዋል።

በዞኑ በተያዘው ዓመት በከፍተኛ ፍርድ ቤት ደረጃ 896 መዝገቦች በቪዲዮ ኮንፍረንስና ኢፋይሊንግ ውሳኔ የተሰጠባቸው መሆኑን በመድረኩ ለውይይት ከቀረበው ጽሑፍ ለማወቅ ተችሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም