ቀጥታ፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2016(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ እና ከፍተኛ የአመራር አባላት ጋር ተወያዩ፡፡

ሊቀ መንበሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድን  ጎብኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማትን ተቀብሎ ማስተናገዱንና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ እና ከፍተኛ የአመራር አባላት ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቋል።

ሙሳ ፋኪ ማህማት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ግቢ እና የስራ ክፍሎች ተዘዋውረው መጎብኘታቸውም ተመላክቷል።


 

ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታና ስኬት ጋር ቅርብ ቁርኝት ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በምስረታው ወቅት የህብረቱ መስራች የነበሩ ታላላቅ የአፍሪካ መሪዎችን ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች በማጓጓዝ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የአየር መንገዱ መረጃ ያመላክታል፡፡


 

ይህ ቁልፍ ሚና ዛሬም አፍሪካውያንን እርስ በርስ ብሎም ከተቀረው ዓለም ጋር ይበልጥ በማስተሳሰር አይተኬ ሚናውን በትጋት እንደሚወጣም ማስታወቁን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም