በአረንጓዴ አሻራ የተያዘው ዕቅድ እስኪሳካ ችግኝ መትከላችንንና መንከባከባችንን አጠናክረን እንቀጥላለን-የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አመራሮችና ሠራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
በአረንጓዴ አሻራ የተያዘው ዕቅድ እስኪሳካ ችግኝ መትከላችንንና መንከባከባችንን አጠናክረን እንቀጥላለን-የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አመራሮችና ሠራተኞች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ የተያዘው ዕቅድ እስኪሳካ ችግኝ መትከላችንንና መንከባከባችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አመራሮችና ሠራተኞች ተናገሩ።
በ2016 ዓ.ም የክረምት ወቅት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በሀገሪቱ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱ ይታወቃል።
ይህም ዕቅድ እውን እንዲሆን የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብሎም ተቋማቶች የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር እየተከናወነ ይገኛል።
በዛሬው እለት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች አያት ኮንዶሚኒየም አካባቢ በመገኘት አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነፃነት ለሜሳ፤ ተቋሙ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በየዓመቱ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
በተለይም ድርጅቱ ባለፉት አራት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን በማካሄድ ተቋሙ የሚያሳርፈውን አስተዋጽዖ ለማሳደግ በደን ያልተሸፈኑ ቦታዎችን የማልማት ሥራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬ መላው የተቋሙ ሠራተኞች በአያት ኮንዶሚኒየም አካባቢ እና በሌሎች የተቋሙ ቅርንጫፎች ባሉበት የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አንደተከናወነ ጠቁመዋል።
ዛሬ በአያት ኮንዶሚኒየም የተለያዩ የእጽዋት ዓይነቶች መተከላቸውን ገልጸው፤ ከእነዚህም ውስጥ የቀርከሀ ችግኝ ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የምንተክላቸው ችግኞች ፍሬያማ እንዲሆኑ ተቋሙ ተገቢውን እንክብካቤ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ቀጣይነት ይኖረዋል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ሁላችንም ዜጎች ለምንተክላቸው እጽዋቶች የመንከባከብና የመጠበቅ ባህላችንን ማጎልበት አለብን ሲሉም አቶ ነፃነት ተናግረዋል።
የመድን ድርጅት ለሚያጋጥሙ ችግሮች ካሳ ከመክፈል ባለፈ ችግሮችን አስቀድመን መከላከል በምንችልባቸው የልማት ሥራዎች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለብን ሲሉም አክለዋል።
በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ ላይ ያገኘናቸው የተቋሙ ሠራተኞች አቶ ካሳሁን ጌታቸው እና አቶ ብርሃኑ ከበደ በበኩላቸው፤ በየጊዜው እንደ ሀገር የምንተክላቸው ችግኞች በአየር ንብረቱ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እየመጣ በመሆኑ አጠናክረን እንቀጥላል ብለዋል።