የቡና የግብይት ስርዓት ያልተማከለ አሰራር እንዲከተል በመደረጉ ትርጉም ያለው ለውጥ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የቡና የግብይት ስርዓት ያልተማከለ አሰራር እንዲከተል በመደረጉ ትርጉም ያለው ለውጥ መጥቷል
ቦንጋ፤ ሀምሌ 16/ 2016 (ኢዜአ)፦በቡና የግብይት ስርዓት ያልተማከለ አሰራር ተግባራዊ በመደረጉ ትርጉም ያለው ለውጥ መመዝገቡን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡና፣ሻይና ቅመማቅመም ባለሥልጣን ገለፀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር "የኢትዮጵያ የቡና ኢንዱስትሪን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ በጋራ እንሰራለን" በሚል መሪ ሃሳብ ከአባላቱ ጋር በቦንጋ ከተማ መክሯል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ እንደገለፁት፤ በቡና የግብይት ስርዓት ያልተማከለ አሰራር ተግባራዊ በመደረጉ ትርጉም ያለው ለውጥ መጥቷል።
ቡና ለሀገሪቱ 35 በመቶ ያህሉን የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ የግብርና ምርት መሆኑን አንስተው ከተለምዷዊ አሰራር ወጥቶ በዘመናዊ እና በተቀናጀ አግባብ መስራት ይገባል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በዘርፉ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸው አንዱ የግብይት ስርዓቱን ያልተማከለ ማድረጉ ሲሆን ይህም ከፍተኛ መነቃቃትና ለውጥ ማምጣቱን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና አቅራቢዎች ማህበር መመስረቱ ለዘርፉ ሌላኛው እፎይታ መሆኑንና በክልሉም ዘርፉን ለማጠናከርና ተሳታፊዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና አቅራቢዎች ፕሬዚዳንት አቶ ፈጠነ የኋላሸት በበኩላቸው፤ ማህበሩ ከዚህ ቀደም በተበታተነ መንገድ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ማህበራት በአንድ ላይ ሆነው የመሰረቱት መሆኑን ገልፀዋል።
ማህበሩ ለሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን ቡና በጥራትና በብዛት ለማቅረብ በግብይት ሰንሰለቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ጤናማ ኢንዱስትሪ መፍጠር ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበትን የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት በተለይም በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተገቢውን ጥቅም በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ስራ መስራት ይገባል ብለዋል።
ችግሮችን በጥናት ለይቶ በመፍታት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ከዲላ፣ ከጅማ እና ከቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የግብ ስምምነት በመፈራረም እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
የብሔራዊ ማህበሩ ስራ አስፈፃሚና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡና አዘጋጆችና አቅራቢዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዝናቡ አባመጫ፣ ማህበሩ ከተቋቋመ ወዲህ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል።
ማህበሩ በተለይ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመነሻቸው በመለየት ከመንግስት ጋር በመቀናጀት በሚፈቱባቸው ጉዳዮች ላይ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የጥራት፣ የገበያ ትስስርና የምርታማነት ችግር በዋነኝነት የተለዩ መሆናቸውን ገልፀው፣ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግስት ችግሮችን በቁርጠኝነትና በተቀናጀ አግባብ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
በመድረኩ የተሳተፉት ሞዴል አርሶ አደር አቶ መስፍን ገብሬ አምስት ሄክታር የቡና ማሳ እንዳላቸው ገልፀው፣ ከገበያ ትስስር ጋር ተያይዞ ከዘርፉ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እያገኙ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
በመድረኩ ከካፋ ዞን የተወጣጡ የቡና አልሚዎች፣ አቅራቢዎች፣ ላኪና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በማህበሩና በዘርፉ ማነቆዎች ዙሪያ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመጨረሻም ለተሳታፊዎች የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።