አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሁሉም ዕዞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ የጤና ተቋማት በመገንባት ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል-ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሁሉም ዕዞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ የጤና ተቋማት በመገንባት ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል-ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
ድሬዳዋ ፤ ሐምሌ 6/2016 (ኢዜአ)፦ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በመከላከያ ሠራዊት ሁሉም ዕዞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ የጤና ተቋማት በመገንባት፣ አዳዲስ አሠራሮችንና አደረጃጀቶች በመዘርጋት ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን የኢፌዴሪ ጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
ድሬዳዋ የሚገኘው የምስራቅ ዕዝ የደረጃ ሶስት ሆስፒታል ለ8ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 800 የጤና ባለሙያዎች ዛሬ ያስመረቀ ሲሆን በምረቃው ላይ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ሌሎች የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖችና ሲቪል አመራር አባላት ተገኝተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ወቅት የአገር መከላከያ ሰራዊት የአገርን ሉአላዊነትና ህግን ከማስከበር ጎን ለጎን ሰራዊቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በተለይም በዘመናዊ የጤና ቴክኖሎጂ የተደራጀ የጤና ተቋማት እና ባለሙያዎች በማፍራት ሠራዊቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በጥራትና በብቃት እየገዘፈ እና እየሰፋ የሚገኘውን የዘመኑን ሠራዊት የሚመጥን የጤና አገልግሎቶች ተደራሽ ማድረግ አሁናዊ እና ወቅታዊ ጥያቄ መሆኑንም አስረድተዋል።
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተለይ ጤናው ዘርፍ በሁሉም ዕዞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ የጤና ተቋማት በመገንባት፣ አዳዲስ አሠራሮችንና አደረጃጀቶች በመዘርጋት ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በድሬዳዋ የሚገኘው የምስራቅ ዕዝ ደረጃ ሶስት ሆስፒታልን የመሳሰሉ ዘመናዊ ሆስፒታሎች በሁሉም ዕዞች እውን እየተደረገ መሆኑን አውስተዋል።
እነዚህ ስራዎች ለሠራዊት ዘመኑን የሚመጥን የጤና ዋስትናና የህክምና ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር ወደ አዲስ አበባ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል የሚደረገውን የቅብብሎሽ ጫና ያስቀራልም ነው ያሉት።
የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ጥጋቡ ይልማ በበኩላቸው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተቀናጀ የሪፍርም ስራዎች በመተግበርና በውጤት በመታጀብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በጤናው ዘርፍ የተጀመረው የሪፎርም ስራ በመለስተኛ የህክምና ዘርፎች በሁሉም ዕዞች ባለሙያዎች በማፍራት ያሉትን ፍላጎቶች መሸፈን ተችሏል ብለዋል።
ከመሠረተ ልማት እና ከቴክኖሎጂዎች ተደራሽነት ጎን ለጎን ለሰው ኃይል ስልጠናና ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት ዛሬ በሠራዊቱ ታሪክ ስምንት መቶ የሚጠጉ ባለሙያዎች በአንድ ጊዜ በማፍራት የመጀመሪያ ውጤቱን ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።
የምስራቅ ዕዝ ደረጃ ሶስት ሪፈራል ሆስፒታል አዛዥ ኮሎኔል ብርሃኑ ዘውዱ፣ ተመራቂዎቹ የተግባር እና የንደፍ ሃሳብ ትምህርታቸውን በታላቅ ብቃት እና ጥራት ያጠናቀቁ ናቸው ብለዋል።
ዛሬ ድሬዳዋ በሚገኘው የምስራቅ ዕዝ የደረጃ ሶስት ሪፈራል ሆስፒታል በተካሄደ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የዕለቱ የክብር እንግዶች በቅጥር ጊቢው የተለያዩ ችግኞች በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
በሆስፒታሉ የሚታየውን የውሃ ዕጥረት ለመፍታት የተገነባውን የጥልቅ ውሃ ፕሮጀክትንም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር መርቀዋል።