በክልሉ በጤና ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶች የተገልጋዩን ፍላጎት ያማከሉ እንዲሆኑ በብቁ የሰው ኃይልና በግብዓት የማደራጀት ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በጤና ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶች የተገልጋዩን ፍላጎት ያማከሉ እንዲሆኑ በብቁ የሰው ኃይልና በግብዓት የማደራጀት ተግባር እየተከናወነ ነው
አዳማ ፤ ሐምሌ 6/2016(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች የህብረተሰቡን ፍላጎት ያማከሉ እንዲሆኑ በህክምና መሳሪያዎችና በብቁ የሰው ኃይል የማደራጀት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ።
ቢሮው ያዘጋጀው 3ኛው የክልሉ የጤና አገልግሎት ጥራት ማስጠበቅ የባለድርሻ አካላት ጉባኤ በአዳማ ተካሄዷል።
የቢሮው ኃላፊ ዶክተር መንግስቱ በቀለ እንደገለፁት፤ በየደረጃው ባሉ የጤና ተቋማት የሚሰጡ ሁሉን አቀፍ አገልግሎቶች ጥራትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
ተቋማቱ አገልግሎቱን ለማሻሻል የህክምና መሳሪያዎችንና የመድኃኒት አቅርቦት እንዲሟላላቸው በማድረግ ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓትና አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዚህም ለአገልግሎት ጥራት ማነቆ የሆኑትን የህክምና መሳሪያዎችና መድኃኒቶች አቅርቦት እጥረትና በዘርፉ የሚስተዋል ብልሹ አሰራር ለማስወገድ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በተቋማቱ በየአገልግሎት ዘርፉ የሚታየውን የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው በዚህም ብቁ ሙያተኞችን የማብዛት ስራም ጎን ለጎን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁንም በጤናው ሴክተር በሚፈለገው ደረጃ የአገልግሎት አሰጣጥና የህክምና ግብዓት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለው ክፍተት በተላላፊ በሽታዎች ሳቢያ እየደረሰ ላለው ጉዳት ምክንያት እየሆነ ነው ብለዋል።
የሙያና የጥራት ደረጃን መሰረት ያደረገና የህብረተሰቡን ፍላጎት ያማከለ የህክምና አገልግሎት መሰጠት ላይ አሁንም ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በበኩላቸው የአገልግሎት ጥራት በዘርፉ ተቋማት ዘንድ ባህል ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በየደረጃው ባሉ የጤና ተቋማት እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶች ከተቀመጠው የጥራት ደረጃ አንፃር መለካትና ክፍተቶችን በመሙላት ተመሳሳይና ወጥነት ያለውን አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ገልፀዋል።
ከበሽታ መከላከል፣ አክሞ እስከ መፈወስ ያለውን ሂደት ያካተተ የሚገመትና የሚለካ አገልግሎት መስጠት ከጤና ተቋማት የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በዚህም የዘርፉን ፖሊሲና ስትራቴጂ ውጤታማ በሆነ መንገድ ከመፈጸም ጀምሮ መዋቅራዊ ለውጥ በጤናው ሴክተር ለማምጣት የሚያስችል ግብ መቀመጡን አመልክተዋል።
ጉባኤው በክልሉ የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥና ግብዓት አቅርቦት ላይ የተካሄዱ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት በማካሄድና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቋል።