በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሪሚታንስ ከ6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ተልኳል 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2016(ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት በሪሚታንስ ከ6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ወደ አገር ቤት መላኩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለጸ። 

የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በሪሚታንስ የሚላከው ገንዘብ ጨምሯል።  

ይህንንም ተከትሎ በተጠናቀቀው የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት በሪሚታንስ ከ6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ወደ አገር ቤት መላኩን ነው የገለጹት።   

 በሌላ በኩል 273 የዳያስፖራ አባላት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ ለማስቻል ተጨባጭ ሥራዎች መሰራታቸውንም ጠቁመዋል። 

ከእነዚህም ውስጥ 50 የዳያስፖራ አባላት ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ ለ3 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል።   

ጎን ለጎንም ዳያስፖራው የታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በሌሎች ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ውስጥ ዋነኛ ተዋናይነቱን በተግባር እያረጋገጠ ነው ብለዋል። 

በቀጣይም የዳያስፖራ አባላት በአገሪቱ በተለያዩ መስኮች የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም