ቀጥታ፡

የግራንድ አፍሪካን ሩጫ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - አትሌት ደራርቱ ቱሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2016(ኢዜአ)፦የግራንድ አፍሪካን ሩጫ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብ አብሮነትን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ገለጹ።

6ኛው የግራንድ አፍሪካን ሩጫ "አብሮነት መሻል ነው" የመዝናኛ ሩጫ በመጪው ጥቅምት በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ ግራንድ አፍሪካን ረን እና ኢምፓክት አዋርድ አፍሪካ በአሜሪካ ባለፉት አምስት ዓመታት ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል።

የዘንድሮው 6ኛ የግራንድ አፍሪካን ሩጫ "አብሮነት መሻል ነው" በሚል መሪ ሃሳብ እ.አ.አ በመጪው ጥቅምት 12/2024 ወይም 02/2017 ዓ.ም በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵውያንም ሀገራቸው በምትታወቅበት የሩጫ ውድድር ከልጆቻቸው ጋር ተሰባስበው ባህላቸውን በአብሮነት የሚያከብሩበት መድረክ በመሆኑ ከፍ ያለ ትርጉም እንዲኖረው ያደርገዋል ብላለች።

ዝግጀቱን በድምቀት እንደምናሳልፍ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ ያለችው ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ በዝግጅቱም  በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዝግጅቱ ላይ እንዲሳተፉ እጋብዛለሁ ብላለች። 


 

የግራንድ አፍሪካን ሩጫ ዋና ዳይሬክተር ጋሻው አብዛ (ዶ/ር) ለኢዜአ በላኩት መግለጫ፤ መርሐ ግበሩ የአንድ ቀን የ5 ኪሎ ሜትር የቤተሰብ መዝናኛ የሩጫ ዝግጅት መሆኑን ገልጸዋል።

በቤተሰብ ሩጫ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና አፍሪካዊያንን በማሰባሰብ ከባህላቸው ጋር የሚተዋወቁበት እና ለተለያየ በጎ ስራ የሚውል ገቢ ማሰባሰቢያ የሚደረግበት ዝግጅት መሆኑን ተናግረዋል።

በዝግጅቱ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚደንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ጨምሮ ሁለት የዓለም ሪከርድ ባለቤት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በክብር እንግድነት እንደሚታደሙ አስታውቀዋል።

በውጭ የምንኖር ኢትዮጵዊያን በስራ ምክንያት ለበርካታ ጊዜያት ሳንገናኝ እንቆያለን ያሉት ዶክተር ጋሻው፤ የግራንድ አፍሪካን ሩጫ ኢትዮጵዊያንን በማሰባሰብ በአብሮነት የምናሳልፍበት ዝግጅት ነው ብለዋል።

በዚህ የቤተሰብ ሩጫ  "ሁሉም አሸናፊ ነው" ያሉት ዳይሬከትሩ፥ በሩጫው የሚሳተፉ ሁሉ ዕድላቸውን የሚሞክሩበት የሎተሪ ዝግጅት ላይ አንድ ዕድለኛ የ2024 ቶዮታ ኮሮላ መኪና እንደሚሸለም ጠቁመዋል።

በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና አፍሪካዊያን የዲያስፖራ አባላት በዝግጅቱ ለመካፈል በ www.africanrun.com ላይ መመዝገብ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

የማራቶን ክበረወሰን ባለቤቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ እና የመካከለኛና የረጅም ርቀት ባለድሏ አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ በዘንድሮው የግራንድ አፍሪካን ሩጫ ዝግጅት እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል።

5ኛው የግራንድ አፍሪካን ሩጫ በጥቅምት 5/2015 ዓ.ም በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት አሌክሳንድሪያ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።

ባለፉት አምስት የግራንድ አፍሪካ የሩጫ ዝግጅቶች ላይ ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ስለሺ ስህን፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ በላይነህ ደንሳሞ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ቁጥሬ ዱለቻ እና ሌሎች ብርቅዬ አትሌቶች በክብር እንግድነት ታድመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም