የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከታክስ በፊት የ25 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከታክስ በፊት የ25 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 05/2016 (ኢዜአ)፡- በ2023/24 የሥራ አፈጻጸም ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታውቋል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ 135 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ13 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ገልጿል።
በዚህ ዓመት ከታክስ በፊት የተገኘው የ25 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ትርፍም በባንኩ ታሪክ ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡን ጠቁሟል።
ለተገኘው ትርፍ ባንኩ የተገበራቸው የወጪ ቅነሳ ስትራቴጂ እና የለውጥ ሥራዎች አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተገልጿል።
የባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠንም ከ1.17 ትሪሊዮን ብር የተሻገረ ሲሆን፤ የደንበኞቹ ቁጥር ደግሞ ከ45 ሚሊዮን በላይ መሆኑን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመልክታል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ ከ218 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት ማቅረቡን ገልጾ፤ ከዚህ ውስጥ 91 በመቶ የሚሆነው ወይም ከ198 ቢሊዮን ብር የሚበልጠው ለግሉ ሴክተር የተለቀቀ ብድር መሆኑን አስታውቋል።
የባንኩ አጠቃላይ የተበላሹ ብድሮች ክምችትም ከፍተኛ መሻሻል በማሳየት በዓመቱ ማጠቃለያ 2 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን ባንኩ ጨምሮ ገልጿል።