ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ ፓስፖርት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የዲዛይን ስራ ተጠናቋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ ፓስፖርት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የዲጂታል ዲዛይን ስራ መጠናቀቁን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ።

የተቋሙ ሀላፊዎች የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምና በ2017 በጀት አመት የሚከናወኑ ተግባራት ላይ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ ሰላማዊት ዳዊት በመግለጫቸውም ተቋሙ በ2016 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ዋና ዋና የለውጥ ተግባራትና እቅድ አፈጻጸም ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም በፓስፖርት አገልግሎት፣ አሰራርን  ከማዘመንና ከተገልጋዮች የሚነሱ ቅሬታዎችን በመፍታት ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ በመግለጫው በዚህ ዓመት አገር ውስጥ የነበረው የቡክሌት መጠን በማነሱ ከፍተኛ ውዝፍ እንደነበር አስታውሰው ችግሩን ለመፍታት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የፓስፖርት ቡክሌት ከውጭ በማስገባት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮኑ ታትሞ ለተገልጋዮች ተደራሽ  መደረጉን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ ከ101 ሺህ በላይ የሚሆነው ፓስፖርት በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተደራሽ መደረጉንም እንዲሁ፡፡

በየዕለቱ ፓስፖርት የማተም አቅምን  ቀደም ሲል ከነበረው 2 ሺህ ወደ 14 ሺህ ማሳደግ መቻሉንም ነው የተናገሩት።

ተቋሙ የሪፎርም ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ 14 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ተናግረው፤ ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ጋር  ሲነጻጻር ሶስት እጥፍ እድገት ያሳየ መሆኑን  አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ በየቀኑ በኦንላን አመልካቾችን የመቀበል አቅም ከ900 ወደ 1 ሺህ 700 ማደጉን ገልጸው፤ በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ በኦን ላይን ማመልከቻን የመቀበል አቅም በአማካኝ 90 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

የኤሌክትሮኒክስ ፓስፖርት ተደራሽ ለማድረግም የዲጂታል ፓስፖርት ዲዛይን ስራ መጠናቀቁን ጠቁመው፤ ይህም ሃሰተኛ ሰነድን ከመከላከል፣ ደንበኞች በተቀላጠፈ መንገድ እንዲስተናገዱ በማድረግ በአጠቃላይ ከፓስፖርት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥነትን ያስቀራል ብለዋል።

ለፖስፓርት ህትመት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ለውጭ አገር ዜጎች የሚሰጠው የመኖሪያ መታወቂያና በውጭ ለሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሰጠው መታወቂያ ላይም በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ እንዲሆን ለውጥ ይደረጋል ብለዋል።


 

የተቋሙ ምክትል ዋና ዳሬክተር ጎሳ ደምሴ በበኩላቸው የመዳረሻ ቪዛ በ188 አገራት ክፍት በተደረገው መሰረት ከ820 ሺህ በላይ የውጭ አገር ዜጎች የቪዛ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ተቋሙ ከ51 ሺህ በላይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች መታወቂያ መስጠቱን ጠቅሰው ከእነዚህ ውስጥ 65 በመቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር)  ጥሪ ተቀብለው የመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለሚኖሩ ከ34 ሺህ በላይ የውጭ አገር ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ላይ የተወሰደውን የማስተካከያ እርምጃም ዘርዝረዋል።

ሃሰተኛ የመኖሪያ ፈቃድ፣ በትውልደ ኢትዮጵያውያን መታወቂያ፣ ቪዛና ሌሎች ሃሰተኛ ሰነዶች ሲገለገሉ የነበሩ ከ18 ሺህ በላይ የውጭ አገር ዜጎች በቅጣት ከአገር እንዲወጡ መደረጉን አብራርተዋል።

 ተቋሙ ከ240 በላይ በህገ-ወጥ ተግባራት ላይ የተሳተፉ ሰራተኞችና ደላሎች ላይ ዕርምጃዎችን መውሰዱን ገልፀው፤ በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ከሲቪል ምዝገባና ሌሎች የ2016 በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራት በመግለጫው የተነሱ ሲሆን በ2017 አገልግሎትን ከማዘመን፣ ምቹ የስራ አካባቢን ከመፍጠር፣ ተደራሽነትን ከማስፋት፣ የተገልጋይ ዕርካታን ከማረጋገጥ አኳያ የተያዙ ዕቅዶች ላይ የተቋሙ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም