ቀጥታ፡

በደብረማርቆስ ከተማ የተገኘው ሠላም የልማት ስራዎች እንዲቀጥሉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል- ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ

ደብረ ማርቆስ/ ወልዲያ፤ ሐምሌ 5/2016(ኢዜአ)፡-በደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር የተገኘውን ሠላም ተከትሎ የልማት ስራዎች እንዲቀጥሉና የአገልግሎት አሰጣጦች እንዲፋጠኑ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ መንበሩ ዘውዴ ገለጹ።

"ሠላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሠላም"  በሚል ሃሳብ ደብረማርቆስ ከተማ የመንግስት ሰራተኞች፤ በወልዲያ ከተማ ደግሞ ነዋሪዎች የተሳተፉበት የሠላም  ኮንፍረንስ ተካሄዷል። 

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ  መንበሩ ዘውዴ በወቅቱ  እንዳሉት፤ እንደ ከተማ አስተዳደር  ብሎም እንደ ክልል በነበር ችግር ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል።


 

ችግሮችን በውይይት መፈታት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የሠላም ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን አውስተው፤  ለካውንስሉ እንቅስቃሴ ውጤታማነትም ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።

እንደ ከተማ አስተዳደር የተገኘውን  ሠላም ተከትሎ የልማት ስራዎች እንዲቀጥሉ፣ የአገልግሎት አሰጣጦች እንዲፋጠኑና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ መሰራቱን አብራርተዋል።

ከኮንፍርንሱ ተሳታፊ የመንግስት ሰራተኞች መካከል  አቶ ታደለ ወርቁ በሰጡት አስተያየት፤ ችግሮችን በሠላማዊ አግባብ  ለመፍታት የተጀመረው እንቅስቃሴ  ለውጤት ማብቃት እንደሚገባ ተናግረዋል።

መንግስት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የጀመረውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ የተናገሩት ደግሞ አቶ ፈቃድ በልስቲ ናቸው።

 ሠላም ተጠብቆ በከተማው የተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ  እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በወልዲያ ከተማ በተካሄደው የሠላም ኮንፍረንስ ላይ የከተማው አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ፤  ለሠላም መጠበቅ  በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ለዚህም የሃይማኖት መሪዎችን፣ የሃገር ሽማግሌዎችንና ሌሎችም  ተሰሚነት ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን  በማወያየት ለሰላም መከበር  እንዲሰሩ እየተደረገ ያለውን ጥረት ጠቅሰዋል። 

ችግሩ በሰላማዊ ንግግር  እንዲፈታ የሚደረገው ጥረት መቀጠሉንና  ለዚህም ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ አመልክተዋል።

ከኮንፍረንሱ የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ውስጥ   አቶ አያሌው አበራ እንዳሉት፤ችግሩን ዘላቂነት ባለው መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት አንዲሳካ የሚደግፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የሠላም ካውንስሉ ላቀረበው  የሠላም አማራጭ መሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በደብረ ማርቆስ ከተማ በተካሄደው የሠላም ኮንፍረንስ የመንግስት ሠራተኞች፤ በወልዲያ ከተማ መድረክ  የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም