ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የወባ በሽታን ለመከላከል የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ነው

ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 5/2016 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የወባ በሽታን ለመከላከል የቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ክልላዊ የወባ በሽታ ምላሽ ክስተት አስተዳደር ግብረ ኃይል የወባ በሽታን ክስተት በማስመልከት ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ እንደገለጹት፤ በክልሉ የተከሰተው የወባ በሽታ በሰው ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ለመከላከል ርብርብ እየተደረገ ነው። 

የወባ በሽታው በክልሉ ጎልቶ በተከሰተባቸው 21 ወረዳዎች በአሁኑ ወቅት ቤት ለቤት የወባ መከላከያ ኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ከ410 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶችን በመርጨት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ከወባ በሽታ ለመጠበቅ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከአንድ ግብረሰናይ ድርጅትና ከጤና ሚኒስቴር የተገኘ 600 ሺህ የአልጋ አጎበርን በ10 ወረዳዎች ለማሰራጨትም የመጓጓዝ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በየአካባቢው ለወባ ትንኝ መራቢያ አመቺ የሆኑ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን ለይቶ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የማፋሰስና የማዳፈን ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አቶ በላይ አስረድተዋል።  


 

በክልሉ የወባ በሽታ ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ያሳሰቡት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊና ክልላዊ የወባ በሽታ ምላሽ ክስተት አስተዳደር ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ ናቸው።

ህብረተሰቡም የአልጋ አጎበር በአግባቡ በመጠቀምና በየአካባቢው ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስና በማዳፈን ራሱን ከበሽታው መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የብዙሀን መገናኛዎች ስለወባ በሽታ አስከፊነት የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ አጀንዳቸው በማድረግ ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም