ቀጥታ፡

የባለ ልዩ የቡና ጣዕም ቅምሻ ውድድር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ የሀገሪቱን የቡና ጥራት እያሳደገ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2016(ኢዜአ)፦ የባለ ልዩ የቡና ጣዕም ቅምሻ ውድድር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ  lቡና ጥራት  ከፍተኛ  አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን  አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማኅበርና ከአሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ጋር በመተባባር አራተኛውን የባለ ልዩ የቡና ጣዕም ቅምሻ ውድድር አካሂዷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ፣ጥራት በማስጠበቅ፣ ግብይትን በማዘመንና እሴት የተጨመረበት ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

ይህንንም አላማ ለማሳካት የልዩ ቡና ጣዕም ቅምሻ ውድድርን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

በውድድሩ ሂደት አርሶ አደሮች ምርታማነትንና ጥራትን በአግባቡ በመጠበቅ አሸናፊ እንዲሆኑ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ብቻ ሳይሆን ለተከታታይ ሶስት አመታት በከፍተኛ ነጥብ ማሸነፍ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ውድድሩ በኢትዮጵያ መካሄዱ የኢትዮጵያን ቡና ለማስተዋወቅና ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት በተካሄዱ ውድድሮች የተለየ ጣዕም ያለው የቡና ዝርያ በሲዳማ አካባቢ መገኘቱን በአብነት አንስተዋል፡፡

ውድድሩ ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የቡና ግብይትን ለማሳደግ የያዘችውን ስትራቴጂ ለማሳካት አጋዥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ አለም አቀፍ የቡና ግብይት ተዋናዮች በአካል የኢትዮጵያን ቡና በመቅመስ የሚስማማቸውን እንዲለዩ እድል የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የካፕ ኦፍ ኤክሰለንሲ የ2024  አስተባባሪ አቶ እንዳለ አስፋው በበኩላቸው ለባለ ልዩ ጣዕም ቅምሻ ውድድሩ የቀረቡ ናሙናዎች በጅማ፣ በሀዋሳ፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ ባሉ ማዕከላት መሰብሰባቸውን ገልጸዋል፡፡

በውድድሩ ከ 20 ሄክታር በታች ያላቸው ከ800 በላይ የቡና አርሶ አደሮች ላለፉት ስድስት ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ መወዳደራቸውና ከእነዚህም ውስጥ 150 ቹ በአለም አቀፍ  ደረጃ እንዲወዳደሩ ተለይተዋል፡፡

በዚህ ሳምንት በተካሄደው ውድድር በአለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን የሚወክሉ 40 አምራቾች መለየታቸውንና ሁለቱ ከ90 ነጥብ በላይ በማግኘት ለፕሬዝደንሻል አዋርድ ከፍተኛ ውድድር ማለፋቸውን ገልጸዋል፡፡

የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር እ.አ.አ በ1999 በብራዚል ተጀምሮ፣ በኮሎምቢያ፣ በፔሩ፣ በኤል ሳልቫዶር ፣በኮስታሪካ፣ በኒካራጉዋ፣ በጓቲማላ፣ በሆንዱራስ፣ በሜክሲኮ፣ በብሩንዲና ሩዋንዳ ሲካሄድ ቆይቷል። 

ተወዳዳሪዎቹ በነሃሴ ወር መጨረሻ በሚወጣው አለም አቀፍ የበየነ መረብ ጨረታ ቡናቸውን በማቅረብ በከፍተኛ ዋጋ እንደሚሸጡ ይጠበቃል፡፡

ከዚህም ቀደም በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ አምራቾች በቡና ላኪነትና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሰማራት ለሀገር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም