በመዲናዋ እየታየ ያለው የጽዳትና ውበት ለውጥ የተቋማት ቅንጅት ውጤት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ እየታየ ያለው የጽዳትና ውበት ለውጥ የተቋማት ቅንጅት ውጤት ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2016(ኢዜአ)፦በመዲናዋ እየታየ ያለው የጽዳትና ውበት ለውጥ የተቋማት ቅንጅት ውጤት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽዳት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባን ጽዳትና ውበት በሚገባው ደረጃ ለመጠበቅ የከተማ አስተዳደሩ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ከከተማዋ የተለያዩ ቢሮዎች ጋር ትስስር በመፍጠር እየሰራ ይገኛል፡፡
በከተማው የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ባለሙያ አቶ ተስፋሁን ታምሩ ፤ባለስልጣኑ በደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ዙሪያ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
ከማዕከል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች የከተማዋን ጽዳት ለማስጠበቅ በቅንጅትና በቁርጠኝነት በሰሩት ስራ በከተማዋ የሚታይ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በህዝብ መድረኮች፣ ቤት ለቤትና በየተቋማቱ በመሄድ የግንዛቤ መፍጠር ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ተስፋሁን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ በከተማዋ ደረቅ ቆሻሻ ያለ ቦታው የሚጥሉ፣ ፍሳሽ ቆሻሻ ያለአግባብ የሚለቁ አካላት ሲገኙ በደንቡ መሰረት እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ነው ያስረዱት።
በመዲናዋ የተጀመረው የጽዳትና ውበት ሥራ ቀጣይነት እንዲኖረው ሁሉም ህብረተሰብ የድርሻውን ሊያበረክት እንደሚገባም አክለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ተስፋአገኘሁ ለገሰ በበኩላቸው ፤ የከተማዋን ጽዳትና ውበት በቀጣይነት ለማስጠበቅ ትምህርት ቢሮው ለተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በዚህም በ829 የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች የአካባቢ ጥበቃ ክበብ በማቋቋም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራቱንና ተማሪዎች ያገኙትን ግንዛቤ በተግባር እንዲያሳዩ በትምህርት ቤታቸው አካባቢ ዘወትር ዓርብ የጽዳት ዘመቻ እንዲኖር መደረጉን አክለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ጽዳት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳዲቅ ሽኩር ፤ አዲስ አበባ የፌዴራልና የአፍሪካ መዲና እንደ መሆኗ ከተማዋን ስማርት ሲቲ ለማድረግ የኮሪደር ልማትና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኤጀንሲዉ በየዕለቱ ከመኖሪያ ቤቶች፣ ተቋማትና ንግድ ቤቶች የሚወጡ ቆሻሻዎችን የመሰብሰብ፣ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግና የማስወገድ ተግባር እያከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የከተማዋን ጽዳትና ውበት ለመጠበቅ የተጀመረው ተግባር የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ኤጀንሲው ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት በሰራው ስራ ለውጥ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡
በከተማዋ 4 ሺህ 992 ብሎኮች መኖራቸውንና በሳምንት ሁለት ጊዜ የጽዳት ስራ እንደሚከናወንባቸው አስረድተዋል ፡፡
በከተማዋ የየተዘረጉትን አስፓልት መንገዶች በሶስት ደረጃ በመክፈል አንደኛ ደረጃ አስፋልት በቀን ሶስት ዙር፣ ሁለተኛ ደረጃ ሁለት ዙር፣ ሶስተኛ ደረጃ አንድ ዙር ጽዳት እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል፡፡