በሩዝ ሰብል ልማት በመሳተፍ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሩዝ ሰብል ልማት በመሳተፍ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራን ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2016(ኢዜአ)፦ የጅማ ዞን ለሩዝ ሰብል ልማት ባለፈው ሰፊ አቅም በመሳተፍ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ እንደሚገኙ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዞኑ ወጣቶች ገለጹ፡፡
ከ4 ዓመት በፊት ወደ ስራ የገባው የብሔራዊ የሩዝ ልማት ስትራቴጂ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሩዝ ምርትና ልማት የሚሆን 30 ሚሊዮን ሄክታር ገደማ መሬት እንዳለ ያስቀምጣል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ እንደ ስንዴ ሁሉ ኢትዮጵያን በቀጣይ 2 ዓመታት በሩዝ ምርት ከአፍሪካ ቀዳሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የሩዝን ምርት ማሳደግ የሚያስችል አቅም እንዳለ ጠቅሰው ምርቱን በተለያዩ አካባቢዎች ለማስፋት እንደሚሰራ አመልክተዋል።
ይህን ተከትሎ በተለያዩ ክልሎች የሩዝ ልማት እየተከናወነ ሲሆን፤ በኦሮሚያ ክልልም ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ በሚገኙ ሶስት ዞኖች ሩዝን የማልማት ኢኒሺዬቲቭ ተቀርጾ ወደ ስራ ተገብቷለ፡፡
ክልሉ ለሩዝ ልማት አመቺ ካላቸው አካባቢዎች መካከል በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙት ጅማ፣ ኢሉዓባቦርና ቄለም ወለጋ ዞኖች ዋነኞቹ ናቸው።
በዞኖቹ የሩዝ ሰብል በአብዛኛው ውሃ በሚያመነጭ መሬት ላይ የሚዘራ ሲሆን፣ ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢ ማመንጨትና የሥራ ዕድልም እየፈጠረ ይገኛል።
በጅማ ዞን አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች በሩዝ ልማት ላይ ተሰማርተው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ኢዜአ በጅማ ዞን በማህበር ተደራጅተው ሩዝ የሚያመርቱ ወጣቶችን የስራ እንቅስቃሴ ቅኝት በማድረግ አምራቾቹን አነጋግሯል።
ወጣት ካሚል አባራያ፤ የግብርና ባለሙያዎች ባደረጉለት ድጋፍ የሩዝ ምርት በሄክታር ከ50 እስከ 60 ኩንታል ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ይናገራል።
በዘንድሮው ዓመት ከሚያገኙት ምርት በመነሳትም በቀጣይ ሰፊ መሬት ላይ ሩዝ ለማመረት እቅድ መያዛቸውን ይናገራል፡፡
ወጣት ጋሊ አባራያ እና ኢብሳ ሚፍታህ ሩዝ ምርት ከዚህ ቀደም ከሚዘሩት የበቆሎ ምርት በተሻለ መልኩ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ተስፋ ሰንቀዋል።
ከዘንድሮው የምርት ዘመን የተሻለ ያለ የሩዝ ምርት እናገኛለን ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።
በጅማ ዞን የኦሞ ናዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አሚን ሼህ ከሊፋ፤ በወረዳው የሩዝ ሰብል ልማት ባለፉት 2 ዓመታት በሙከራ ደረጃ ሲሰራበት መቆየቱንና አርሶ አደሩ በራስ አቅም ዘር መዝራት መጀመሩን አመልክተዋል።
አርሶ አደሩ የሩዝ ምርትን የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በውል በመገንዘብ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተያዘው ዓመት ሩዝን በክላስተር ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ጠቁመዋል።
የጅማ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ መሃመድ ጠሃ አባፊጣ በዞኑ የሩዝ ልማት ስራ በ2012/13 የምርት ዘመን በ2 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መጀመሩን አስታውሰዋል።
በዘንድሮው የመኸር እርሻ ወቅት 326 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ ምርት ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን 80 በመቶ በዘር መሸፈኑን ጠቁመዋል።
በኦሮሚያ ክልል ከሶስት ዓመት በፊት ከ6 ሺህ ሄክታር መሬት በታች የተጀመረው የሩዝ ልማት ኢኒሼቲቭ በ2015 ዓ.ም ከ700 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ መድረሱን የክልሉ የግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
በተያዘው ዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሩዝ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 1 ሚሊዮን 280 ሺህ 521 ሄክታር መሬት በላይ በዘር መሸፈኑን አመልክቷል።