የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል-ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል-ኢንስቲትዩቱ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2016(ኢዜአ)፦ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ ስርጭቱ እየተጠናከረ እንደሚሔድ አስታውቋል።
የሚጠበቀው እርጥበት የመካከለኛ ጊዜ ሰብሎችን ለመዝራት ፣በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የመኸር ሰብሎች የውሃ ፍላጎትን ለማሟላት እንደሚረዳ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ነው ያስታወቀው።
በዚሁ ወቅት በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን፣ በመካከለኛው እና በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ስፍራዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከ 30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ ዝናብ እንደሚጠበቅም ነው የገለፀው።
በኦሮሚያ፣ አማራ፣ አዲስ አበባ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ አመላክቷል፡፡
በዚሁ የክረምት ወቅት የሚኖረው እርጥበት የሰብሎችን የውሃ ፍላጎት ለማሟላት፣ የግብርና ተግባራትን ለማከናወን፣ ለመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ለግጦሽ ሳር ልምላሜም አዎንታዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስታውቋል።
እንዲሁም በተፋሰሶች ያለውን የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ ሃብትን ከማሻሻል እና የግድቦችንና የወንዞችን የውሃ መጠን ከማሳደግ አንጻር አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚኖረው ከባድ ዝናብ በማሳዎች ላይ የውሃ መተኛት፣ የአረም መስፋፋት ሊከሰት እንደሚችልም አመልክቷል።
በተጨማሪም ከእርጥበት ጋር የተያያዙ የሰብል በሽታዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ቅድመ ዝግጀት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡
የሚኖረው ዝናብ ከሚኖረው ጠቀሜታ ባሻገር ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ነው ኢንስቲትዪቱ ያሳሰበው ፡፡