የ2016 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የአጠቃላይ ካውንስል አባላት በማለፊያ ውጤቱ ዙሪያ ውይይት በማድረግ የማለፊያ ነጥቡን ይፋ አድርገዋል።

በዚሁ መሰረት የ2016 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ከተማ አቀፍ ፈተና የማለፊያ ነጥብ 50 እና ከዚያ በላይ ሆኗል።

ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ደግሞ 45 እና ከዚያ በላይ እንዲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የአጠቃላይ ካውንስል አባላት በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር) የ2016 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ከተማ አቀፍ ፈተና በአጭር ጊዜ ታርሞ ይፋ መደረጉ ተማሪዎች ለቀጣዩ የትምህርት አመት ከወዲሁ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚያስችል ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ ጥቂት ቀናት የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት በተመሳሳይ ይፋ የሚደረግ መሆኑንም ማሳሰባቸውን የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

በ2016 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 85ሺህ 219 በመንግስትና በግል ትምህርት ቤቶች በቀን እና በማታ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ ተማሪዎች መካከል 67ሺህ 903 የሚሆኑት ማለትም 78.9% ያህሉ 50% እና ከዚያ በላይ ማምጣታቸውን በቢሮው የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ዲናኦል ጫላ አስታውቀዋል።

ተማሪዎች ከዚህ በታች ያለውን ማስፈንጠሪያ በመጫን መለያ ቁጥርና ስም በማስገባት ውጤታቸውን መመልከት እንደሚችሉም ቢሮው አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም