ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የገበያ ማዕከላት የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ከግል ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመሥራት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የገበያ ማዕከላት የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድርግ ከሁለት የግል ድርጅቶችጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ሥምምነት ተፈራረመ።

ሥምምነቱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ቢኒያም ምክሩ፣ የሀብ ቢዝነስ  ዋና ስራ አስኪያጅ አማረ ኃልየ፣ የኢትዮ ፅዳትና ጥበቃ አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለማ ልሳኔ ፈርመውታል። 

ሥምምነቱ የለሚኩራና የኮልፌ የገበያ ማዕከላትን ለ3ኛ ወገን በማስተላለፍ የአስተዳደር፣ የጽዳትና የጥበቃ የአገልግሎት ሥራዎችን ለማሰራት ያለመ መሆኑን ተገልጿል።  

ሥምምነቱ የገበያ ማዕከላቱ ደረጃቸውን ጠብቀው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል ተብሏል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ቢኒያም ምክሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የገበያ ማዕከላትን በመገንባት አምራቾችንና ሸማቹን የኅብረተሰቡ ክፍል በቀጥታ ለማገናኘት እየተሰራ ነው።


 

በመዲናዋ በተገነቡ ትልልቅ የገቢያ ማዕከላት የሰብል፡ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶች ለኅብረተሰቡ በተመጣጣይ ዋጋ እንዲደርስ ማስቻላቸውንም ጠቁመዋል።  

የገበያ ማዕከላቱ ከሌላው ገበያ ጋር ሲነፃጸሩ ከ15 እስከ 20 በመቶ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ ግብይት እንደሚፈጽሙ አስረድተዋል። 

የገበያ ማዕከላቱ ቀጣይነት ባለው መልኩ ደረጃቸውን ጠብቀው ጥረት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ዛሬ ከግል ድርጅቶች በጋር ለመሥራት የተደረሰው ሥምምነት የዚሁ አካል ነው ብለዋል።

ሥምምነቱ ድርጅቶቹ የገበያ ማዕከላቱን በማስተዳደር፡ ፅዳታቸውንና ደኅንነታቸውን በማስጠበቅ ለኅብረተሰቡ ደረጃው የጠበቀና የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድርግ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል። 


 

የሀብ ቢዝነስ  ዋና ስር አስኪያጅ አማረ ኃልየ በበኩላቸው በሥምምነቱ መሰረት አማራቾችና ሸማቾች በገበያ ማዕከላት ደረጃዉን የጠበቀ የግብይ ሥርዓት እንዲከናወን ቁጥጥርና የክትትል ሥራዎችን እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 


የኢትዮ ፅዳትና ጥበቃ አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለማ ልሳኔ የገበያ ማዕከላት ጽዳታቸውና ደኅንነታቸው ተጠብቆ አምራቾችና ሸማቾች ያለምንም ችግር ግብይታቸውን እንዲፈጽሙ በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም