የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በጋራ ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በጋራ ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2016(ኢዜአ)፦ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋራ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ሃይለሚካኤልና የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ፈርመውታል።
ስምምነቱ በዋናነት በአመራር ልማት፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በልምድ ልውውጥ ላይ ትኩረት ያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።
በተጨማሪም እንደ አገር ተግባራዊ እየተደረገ ላለው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ስለመሆኑም ተነስቷል።
በአካዳሚው የሚሰጡ ስልጠናዎች የአመራር ብቃትና አቅምን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያግዝ በመሆኑ ለልማት ድርጅቶች ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታልም ተብሏል።
ስምምነቱ አካዳሚው በአመራር ልማት የላቀ ልምድ ካላቸው የአውሮፓና የአፍሪካ አገራት ጋር በቅንጅት እየሰራ ባለበት ወቅት መካሄዱ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በዚሁ ወቅት ተገልጿል።