ቀጥታ፡

የስትራቴጂክ መጠባበቂያ ክምችት አቅምን ወደ 47 በመቶ የሚያሳድጉ ዘመናዊ የክምችት መጋዘኖች እየተገነቡ ነው - የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2016(ኢዜአ)፦ በሀገር አቀፍ የስትራቴጂክ መጠባበቂያ ክምችት አቅም ከ23 በመቶ ወደ 47 በመቶ የሚያሳድጉ ዘመናዊ የክምችት መጋዘኖች እየተገነቡ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት  አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። 

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት  አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)፥ የመፈጸም አቅምን በማሳደግ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን በሚል ስኬታማ የአሰራር ማሻሻያ ሥርዓት መዘርጋት መቻሉን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የተረጅነት አስተሳሰብ ስንፍና እንዲስፋፋ በማድረግ  ፈጠራን የሚያቀጭጭ እና ታታሪነትን የሚጎዳ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ከኢትዮጵያዊነት ባህልና ማንነት ያፈነገጠ ድርጊት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ መነሻነት በአዲስ መልክ ስራ የዋለው የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ የዜጎችን የምርታማነት አስተሳሰብ ልዕልና በማጎናጸፍ የተረጂነት ባህልን ለመሻገር መሰረት እንደሚሆን አንስተዋል።  

በመጠባበቂያ ፈንድ የገቢ አቅምን በማሳደግ መንግስት ከሚመድበው ሃብት ባሻገር ህብረተሰቡ ሚናውን የሚወጣበት የአሰራር ሥርዓት መሆኑን ገልጸዋል።   

በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጋዘን ክምችት አቅም 23 በመቶ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በአማራ እና በሶማሌ ክልሎች ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የክምችት መጋዘኖች እየተገነቡ ነው ብለዋል።

በሆሳዕና፣ ፍኖተ-ሰላምና ቀብሪ-ደሃር ከተሞች በግንባታ ሂደት የሚገኙት ዘመናዊ የክምችት መጋዘኖች ሲጠናቀቁም የስትራቴጂክ መጠባበቂያን የመያዝ አቅም ወደ 47 በመቶ ማድረስ እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።  

በስራ ላይ የዋለው ፖሊሲም የሀገርን ሉዓላዊ ነፃነት እና የዜጎችን ክብር በማስጠበቅ አደጋን በራስ አቅም ምላሽ በመስጠት የክምችትና የመጠባበቂያ ፈንድ አቅምን ማጎልበት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

በመጠባበቂያ ፈንድ በቅድመ አደጋ፣ በአደጋ ወቅት እና ከአደጋ በኋላ ለሚሰሩ ስራዎች በማንኛውም ወቅትና ሁኔታ ለችግር ምላሽ ሚሰጥበት ሃብት የመፍጠሪያ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የማህበረሰብን የመረዳዳት ባህል በማጎልበት በቅድመ አደጋ፣ በአደጋ እና ከአደጋ በኋላ ለሚሰሩ ተግባራት ከ500 ሺህ በላይ ሜትሪክ ቶን የስትራቴጂክ መጠባበቂያ አቅም ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በፌደራል ደረጃ 150ሺህ ሜትሪክ ቶን የስትራቴጂክ መጠባበቂያ ሃብት በማከማቸት ቀሪውን ክልሎች እንደየ አካባበያቸው ጸጋ ማልማት የሚችሉበትን ሥርዓት እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የአደጋ ስጋት ተጋላጭነትን በመቋቋም በትብብርና ትስስር ላይ የተመሰረተ የአይበገሬነት ግንባታም ሌላኛው በተቋሙ አደጋን በራስ አቅም ምላሽ የመስጠት ወሳኝ የትኩረት መስክ መሆኑን ገልጸዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም