4ኛው የባለልዩ ቡና ጣዕም ቅምሻ ውድድር በአዲስ አበባ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
4ኛው የባለልዩ ቡና ጣዕም ቅምሻ ውድድር በአዲስ አበባ ተካሄደ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማኅበርና ከአሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ጋር በመተባባር 4ኛውን የባለ ልዩ የቡና ጥዕም ቅምሻ ውድድር ዛሬ አካሂዷል።
በውድድሩ እያንዳንዳቸው ከ20 ሄክታር በታች ያላቸው ከ800 በላይ የቡና አርሶ አደሮች ላለፉት 6 ወራት መወዳደራቸውና ከእነዚህም ውስጥ 150ዎቹ ለአገር አቀፍ ውደድር ማለፋቸው ተገልጿል።
የተወዳዳሪዎች ናሙና ከጅማ፣ ሃዋሳ፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ መሰብሰቡም እንዲሁ።
ዛሬ በተካሄደው 4ኛው የባለልዩ ቡና ጣዕም ቅምሻ ውድድር 40 አርሶ አደሮች የተቀመጠላቸውን መስፈርት በመሟላት ለዓለም አቀፍ የዘርፉ ውድድር ማለፋቸው ተጠቁሟል።
ምርጥ 40 ተወዳዳሪዎቹ 12 ዓለም አቀፍ ገዢዎች በተገኙበት የተለዩ ናቸው።
የውድድሩ አሸናፊዎችም በቀጣይ ነሐሴ መጨረሻ በበይነ መረብ በሚወጣ የቡና ጨረታ ምርታቸውን በከፍተኛ ዋጋ እንደሚሸጡና ላመጡትም ውጤት ሽልማት እንደሚሰጣቸው ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ የባለ ልዩ የቡና ጣዕም ውድድር በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት ተካሄዷል።
ውድድሩ በተለይ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረጉም በተጨማሪ የሀገሪቱን የቡና ጥራትን ከማሳደግ አንጻር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ነው የገለጹት።
ለአብነትም በ3ኛው የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ በ2014 ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ቡና በጥራቱ ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገብ በዓለም ዓቀፍ ኦንላይን ጨረታ አሸናፊ በመሆን አንድ ኪሎ ግራም ቡና 884 ነጥብ 10 ዶላር መሸጡን አስታውሰዋል።
በ4ኛው የባለልዩ ቡና ጣዕም ቅምሻ ውድድር ባሻ በቀለ፣ ማቲዎስ ለሜሳና ቡኩቶ ዱሬ ከአንደኛ አስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በቅደምተከተል ይዘው አጠናቀዋል።
የባለልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር ቡና የሚያቀርቡ አርሶ አደሮች የቡና ምርታቸው የተሻለ ዋጋ እንዲኖረው ማስቻልን አላማ ያደረገ ነው።
ውድድሩ የኢትዮጵያ ቡና የገበያ መዳረሻን በማስፋት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይገለጻል።
የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር እ.አ.አ በ1999 በብራዚል ተጀምሮ፣ በኮሎምቢያ፣ በፔሩ፣ በኤል ሳልቫዶር፣ በኮስታሪካ፣ በኒካራጉዋ፣ በጓቲማላ፣ በሆንዱራስ፣ በሜክሲኮ፣ በብሩንዲና ሩዋንዳ ሲካሄድ ቆይቷል።
የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከአሜሪካው ተራድኦ ተቋም ‘ፊድ ዘ ፊውቸር’ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ የቡና ጥራት በዓለም አቀፍ ዳኞችና በኢትዮጵያውያን ተሳትፎ የሚካሄድ ‘ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ’ በመባል የሚታወቀውን የልዩ ጣዕም ቡናዎች የቅምሻ ውድድር ወደ ኢትዮጵያ አምጥቷል።