በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን በመደገፍ ለስኬታማነቱ የበኩላችንን እንወጣለን- የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን በመደገፍ ለስኬታማነቱ የበኩላችንን እንወጣለን- የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች
ሰቆጣ ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን በመደገፍ ለተግባሩ ስኬታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
"ሰላም ለሁሉም ፤ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ በሰቆጣ ከተማ የነዋሪዎች የሰላም ኮንፈረንስ ተካሄዷል።
የመድረኩ ተሳታፊ ቄስ ግርማወይ ካሴ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሚደረጉ ጥረቶችን ሁሉም መደገፍ ይገባቸዋል።
መንግስት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ያሳየው ቁርጠኝነት የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልፀው፤ "እኛም ይህንን እሳቤ በተግባር እንደግፋለን" ብለዋል።
ሌላው ተሳታፊ አቶ ረጃ ደባሹ በበኩላቸው፤ ያጋጠመውን የሰላም መታጣት ችግር በሰላማዊ መንገድ መፍታት የህዝብ ፍላጎትና ጥያቄ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ ያጋጠመውን የሰላም መታጣት ችግር ለማቃለል እየተደረጉ ላሉ ጥረቶች አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርጉም ገልፀዋል።
ችግሮችን እና አለመግባባቶችን በሰላማዊ ውይይት የመፍታት ልምድ ሊጠናከር ይገባል ያሉት ወይዘሮ እቴኑ አድማሴ፤ ወገኖች ለሰላም ክብር ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሃጂ ሰለሞን መሃመድ በበኩላቸው፤ መንግስት ለሰላም ያሳየውን ቁርጠኝነት ወደ ተግባር ለመቀየር እያሳየ ያለውን ተነሳሽነት አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
እኛም በሃሰተኛና በተዛቡ መረጃዎች ሳንበረዝ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት ልናግዝ ይገባል በማለት አብራርተዋል።
የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ መላሽ ወርቃለማው እንደገለፁት፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።
በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ህዝቡ ሊያግዝና ሊያበረታታ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በከተማው በተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ነጋዴዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ ኮንፈረንሱም የከተማውን የሰላም ካውንስል አባላት በመምረጥ ተጠናቋል።