የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በማስፋት ዜጎች የሚያገኙትን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በማስፋት ዜጎች የሚያገኙትን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በማስፋት ዜጎች የሚያገኙትን አገልግሎት ግልጽ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ መንግሥት ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚመራበትን የዲጂታል መንግሥት ስትራቴጂና የመንግሥት ኢንተርፕራይዝ አርክቴክቸር የጥናት ሠነድን በተመለከተ ውይይት አካሂዷል።
በመድረኩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ 21ኛውን ክፍለ ዘመን የሚመጥን ዲጂታል መሰረተ-ልማት ለመገንባት በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።
ለዚህም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በመቅረጽ የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ማሳለጥ የሚያስችሉ የለውጥ እርምጃዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ልማት በዜጎች ተሳትፎ የመንግሥትን አገልግሎት ግልጽና ቀልጣፋ በማድረግ የመንግሥትን የመፈጸም አቅም እያጎለበተ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንን ስትራቴጂ መሰረት በማድረግ በቀጣይ አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን የዲጂታል መንግሥት ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር)፤ የዲጂታል መንግሥት ስትራቴጂና ኢንተርፕራይዝ ሰነድ ለአንድ ዓመት ያክል ሲዘጋጅ መቆየቱን ገልጸዋል።
መድረኩም አጋር አካላትን በመጋበዝ በስትራቴጂ ሰነዱ ላይ መካተት የሚገባቸውን ግብዓቶች በመጨመር ስትራቴጂው መጽደቅ የሚችልበትን ምዕራፍ ለማጠናቀቅ ያለመ ነው ብለዋል።
ስትራቴጂ ሰነዱ የዜጎችን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የመንግሥት አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሁም ግልጸኝነት የተላበሰ በማድረግ አገልግሎት አሰጣጡን ለማጠናከር ያለመ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት የትብብር ኃላፊ ሮቤርቶ ሺሊሮ፤ ኅብረቱ በዜጎች ኑሮ ላይ ተጨባጭ ለውጥ በሚያመጡ የኢኮኖሚ መስኮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለው የዲጂታል ሥርዓት ግንባታ የገበያውን ሥርዓት በማቅናትና በማሳለጥ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አዎንታዊ አበርክቶ ይዞ እንደሚመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በመድረኩም ስትራቴጂ ሰነዱን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።