በአቶ አገኘሁ ተሻገር የተመራ ልዑክ ለብሪክስ አባል ሀገራት በተዘጋጀ ፓርላሜንታዊ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ሩሲያ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
በአቶ አገኘሁ ተሻገር የተመራ ልዑክ ለብሪክስ አባል ሀገራት በተዘጋጀ ፓርላሜንታዊ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ሩሲያ ገባ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር የተመራ ልዑክ ለብሪክስ አባል ሀገራት በተዘጋጀ ፓርላሜንታዊ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ሩሲያ ገብቷል፡፡
ጉባኤው በሩሲያ ሰይንት ፒተርስበርግ ከተማ የተዘጋጀ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ጉባኤው እ.አ.አ ሐምሌ 11 እና 12/2024 የሚካሄድ ሲሆን በዛሬው ውሎው የብሪክስ/BRICS/ ሀገራት በተለያዩ የባለ ብዙ ወገን የግንኙነት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እየመከረ መሆኑም በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
በዚህ ጉባኤ የአባል ሀገራቱን ትብብር እና ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚረዳ ፕሮቶኮል እና በጋራ መሥራት የሚያስችል ስምምነት መፈረሙም እንዲሁ፡፡
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያን ፓርላማ አቋም እና የግንኙነት ዝግጁነትን በተመለከተ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር አማካኝነት ገለጻ መደረጉም ተመላክቷል፡፡
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲ፣ ቀጣይነት ያለው እድገት፣ ዘላቂ ሰላም እና ደህንነት ትኩረት የሰጡባቸው ነጥቦች መሆናቸውም ተጠቁሟል።
አፈ ጉባኤው የኢትዮጵያ ፓርላማ የተሳታፊነት ብቻ ሳይሆን የመሪነት ሚናውን ጭምር በብቃት እንደሚወጣ አክለው ማመላከታቸውም ተገልጿል፡፡
መድረኩ በሁለት ቀን ውሎው በእነዚህና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መክሮ ቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም የምክር ቤቱ መረጃ ይጠቁማል።