ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኢትዮጵያ ቡና በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግና ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኢትዮጵያ ቡና በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግና ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኢትዮጵያ ቡና በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግና ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚገጥሟቸው ክለቦች ታውቀዋል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ (ካፍ) የ2024/25 የውድድር ዓመት የሁለቱን አህጉራዊ የክለቦች ውድድር የቅደመ ማጣሪያ መርሐ ግብሮችን ዛሬ ይፋ አድርጓል።
በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያን በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚወክለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጀመሪያው ዙር ከዩጋንዳው ቪላ ክለብ ጋር ይጫወታል።
በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ንግድ ባንክ የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑ ይታወቃል።
የዩጋንዳው ቪላ ክለብ የዩጋንዳ ፕሪሚየር ሊግን 17 ጊዜ እንዲሁም የዩጋንዳ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን 9 ጊዜ አንስቷል። 3 ጊዜ ደግሞ የሴካፋ ክለቦች ዋንጫ ከፍ አድርጓል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደርሶ መልስ ተጋጣሚውን ካሸነፈ በሁለተኛው ዙር ከብሩንዲው ቪታሎና ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ቡና በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በመጀመሪያው ዙር ከኬንያ ፖሊስ ክለብ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።
ኢትዮጵያ ቡና የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዋንጫ ባለቤት በመሆኑ ይታወቃል። ተጋጣሚው ኬንያ ፖሊስ የዘንድሮው የኬንያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊ ነው።
በነጻነት ክብሬ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና በደርሶ መልስ ውጤት ተጋጣሚውን ካሸነፈ በሁለተኛው ዙር ከግብጹ ዛማሌክ ክለብ ጋር ይጫወታል።
ዛማሌክ የወቅቱ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አሸናፊ ነው።
ሁለቱ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ክለቦች ከነሐሴ 10 እስከ 12 የመጀመሪያ ዙር፣ ከነሐሴ 17 እስከ 19 መካከል ባሉ ቀናት ደግሞ የመልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ከ47 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ 59 ክለቦች እንዲሁም በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከ41 ሀገራት የተወጣጡ 52 ክለቦች እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) አስታውቋል።