የግብርናን ዘርፍ ዘመናዊና ምርታማ ለማድረግ የፈጠራ ስራ ሃሳቦችን ይዘው በመቅረብ አሸናፊ የሆኑ ወጣቶች ተሸለሙ - ኢዜአ አማርኛ
የግብርናን ዘርፍ ዘመናዊና ምርታማ ለማድረግ የፈጠራ ስራ ሃሳቦችን ይዘው በመቅረብ አሸናፊ የሆኑ ወጣቶች ተሸለሙ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦ የግብርናን ዘርፍ ዘመናዊና ምርታማ ለማድረግ የፈጠራ ስራ ሃሳቦችን ይዘው በመቅረብ ተወዳድረው ያሸነፉ ወጣቶች ከ3 ሺህ 500 እስከ 10 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ሆኑ።
"ኢፈር" የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያካሔደው ''አዩቴ'' (አግሪካልቸር ዩዝ ኤንድ ቴክኖሎጂ) የፈጠራ ስራ ውድድር ተጠናቋል።
የውድድሩ ዓላማ ወጣቶች እውቀታቸውን ተጠቅመው ግብርናን የሚያዘምኑ የፈጠራ ስራዎችን እንዲያበረክቱ ለማድረግ መሆኑ ታውቋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢፈር ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ቴዎድሮስ የሺወርቅ፤ ኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ አመቺ መልክአ ምድርና የአየር ንብረት ቢኖራትም የምርት መጠኗ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የፈጠራ የውድድሩ ዓላማ ወጣቶች በእውቀታቸው ግብርናን የሚያዘምኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን እንዲያበረክቱ መሆኑን ገልጸዋል።
"ኢፈር" የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም በግብርና ምርትና ቴክኖሎጂ ላይ የሚሰራ በመሆኑ በአገሪቱ የተለያዩ ስራዎችን ከማከናወን ባሻገር ወጣቶች በዘርፉ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶችን እንዲያመርቱ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የዛሬው ውድድርም ለግብርና ዘርፍ እድገትና ምርታማነት የዘመኑ የፈጠራ ውጤቶችን ስራ ላይ ለማዋል መሆኑን ተናግረዋል።
በውድድሩ አንደኛ የወጣው የፈጠራ ስራ 10 ሺህ ዶላር፣ ሁለተኛ የወጣው 6 ሺህ 500 ዶላርና ሶስተኛ የወጣው ደግሞ 3 ሺህ 500 ዶላር ተሸላሚ ሆነዋል።
በውድድሩ በጋራ 1ኛ የወጡት ወጣት ሀመረ ጋሻው፣ ኬብሮን ግዛቸው እና ማርታ ሳሙኤል አውቶማቲክ የእንቁላል ማስፈልፈያ ማሽን በመስራታቸው ነው።
የፈጠራ ሃሳቡ የእቁላል ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የሚያግዝ ፈጠራ መሆኑንም ወጣት ሀመረ ተናግራለች።
በአሁኑ ወቅት ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ማስፈልፈያ ማሽኖች በ18 ቀናት ውስጥ የሚፈለፈልና የማይፈለፈለውን እንቁላል የሚለዩ መሆናቸውን አስታውሳ የእነርሱ የፈጠራ ማሽን ግን በአምስት ቀናት ብቻ መለየት የሚያስችል መሆኑን ገልፃለች።
በመሆኑም የፈጠራ ስራቸው አንደኛ በመውጣት የ10ሺ ዶላር ተሸላሚ በመሆናችን ሁላችንም ተደስተናል ብላለች።
እንሰት በቀላሉ እንዲብላላ በማድረግ ረጅም ጊዜ ይፈጅ የነበረውን የቆጮና ቡላ ምርት በጥራት ባጠረ ጊዜ ለማምረት የሚያስችል ማሽን በመስራት ሶስተኛ የወጣው ወጣት ደሳለኝ ዲባባም በሽልማቱ መደሰቱን ተናግሯል።
ከእንሰት የሚገኘው የቆጮና ቡላ ከፍተኛ የሰው ጉልበት የሚወጣበት ከመሆኑ ባሻገር እንዲብላላ በጉድጓድ ውስጥ ለሁለት ወራት እንዲቆይ የሚደረግ መሆኑን አንስቷል።
የእርሱ ፈጠራ ግን በሁለት ሳምንት ጊዜ ከእንሰቱ ላይ ቆጮውንና ቡላውን በመለየት በጥራት እንዲመረት ከማስቻሉ ባሻገር ድካምና እንግልትን የሚያስቀር መሆኑን ገልጿል።
በመሆኑም በውድድሩ ባገኘው 3 ሺህ 500 ዶላር ሽልማት ማሽኑን በብዛት በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርበ አረጋግጧል።
በስራና ክህሎት ሚኒሰቴር የፈጠራ ሃሳቦች ማበልጸጊያና ኢንተርፕረነርሺፕ ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ ብርሃኑ አደሬ፤ መንግስት የስራ እድል ፈጠራ አማራጮችን ለማስፋት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሚፈጠሩ የስራ እድሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ያማከሉ እንዲሆን በዘርፉ ከሚሰሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።