ቀጥታ፡

በአገሪቱ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ዜጎች በተለያዩ የኃይል አማራጭ ቴክኖሎጂዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦ከግማሽ ሚሊየን በላይ ዜጎች በተለያዩ የኃይል አማራጭ ቴክኖሎጂዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ኃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል። 


 

በመድረኩ ላይ የክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ የልማት አጋሮች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የግል አልሚዎችና ሌሎች በዘርፉ ላይ የተሠማሩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ኃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ ነው። 

ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ዜጎች በተለያዩ የኃይል አማራጭ ቴክኖሎጂዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በተጓዳኝም፤ የውኃ አቅርቦትን ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ መንግሥት ከሚያደርገው በጀት በተጨማሪ የልማት አጋሮች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።

በቀጣይም የውኃና የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ጠቁመዋል። 

መድረኩ በጋራ እንዴት መሥራት እንደሚቻል፣ ኃብት የማሰባሰብ እንዲሁም ከተከናወኑ ሥራዎች ልምድ የሚወሰድበትና ቀጣይ ሥራዎች የሚመላከቱበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው፤ ዘርፉ ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ የሚፈስበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘርፉ በጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት እንደሚመራ ተናግረዋል።


 

ዘርፉ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢውም ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያደርግ መሆኑንም አንስተዋል።

የልማት አጋሮች በዘርፉ ተሳትፏቸውን ለማጠናከር ምቹ መደላደል እየተፈጠረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ንጉሱ ለገሰ (ዶ/ር) ናቸው።


 

በዚህም በተሰማሩበት መስክ የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተናገሩት።

መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በዘርፉ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች እየመከረ ነው።  

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም