ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ቻይና በኢኮኖሚ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቻይና በኢኮኖሚ ዘርፍ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ከቻይና ዓለምአቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ ሰብሳቢ ላዎ ዣሆኢ ጋር በቤጂንግ ተወያይተዋል።

ሁለቱ የስራ ሃላፊዎች በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል በኢኮኖሚ ልማቱ ያለውን ጠንካራ ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት ተስማምተዋል።

በውይይቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያከናወነቻቸውን አመርቂ ውጤቶች ለሰብሳቢው ያስረዱ ሲሆን በተለይ ለወጣቶች በርካታ የስራ እድል መፈጠሩንና ኢኮኖሚውን ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ መደረጋቸውን አብራርተዋል።

ሚኒስትሩ የቻይና ዓለምአቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ በተለይ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ በስኬት መከናወኑን ገልጸው ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች በተለይ ለቻይና ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለመፍጠር በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

አቶ መላኩ በማዕድን፣ግብርናና አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተከናወኑ ስራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በዘርፎቹ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው የአረንጓዴ ልማት ስራን አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት ሚኒስትሩ በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ ዓለምአቀፍ ችግሮችን ለመፍታት የጋራ ርብርብ እንደሚያስፍግ አመላክተው ቻይናን ጨምሮ ዓለምአቀፍ አጋር አካላት በዘርፉ ያላቸውን ትብብር እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የቻይና ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ ሰብሳቢ ላዎ ዣሆኢ በበኩላቸው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ ስለመሆኗ ተናግረዋል።

የቻይና ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት እንቅስቃሴን ለመደገፍ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመተግበር እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

ከሁለትዮሽ ውይይቱ ባሻገር የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ተወካይ የተገኙበት የሶስትዮሽ ውይይት የተደረገ ሲሆን የጋራ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ ሰነዶች መፈረማቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመረጃው አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም