ጽዱ ሀገርና ጤናማ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ሊያግዝ ይገባል - ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ - ኢዜአ አማርኛ
ጽዱ ሀገርና ጤናማ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ሊያግዝ ይገባል - ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጽዱ ሀገርና ጤናማ ማኅበረሰብን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ሊያግዝ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ አሳሰቡ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በክረምት ወቅት ከወከላቸው ሕዝብ ጋር በሚኖራቸው ቆይታ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ፣ የምክር ቤት አባላትና የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባን ጨምሮ የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የማኅበረሰብ ጤናን ለማጎልበት የሚሰሩ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች እያስገኙ ነው።
በተያዘው ክረምት ወቅት አባላቱ ከወከሉት ማኅበረሰብ ጋር በሚኖራቸው ቆይታ በጤና አገልግሎት፣ ተደራሽነት፣ ጥራትና መድኃኒት አቅርቦትን ጨምሮ በዘርፉ የሚነሱ የኅብረተሰቡ ጥያቄዎችን መለየት አንዱ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም አባላቱ በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም እና የሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄዎች እንዲፈቱ በየደረጃ ካሉ አመራሮች ጋር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የጤናውን ዘርፍ ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ደረጃ ጋር ለማጣጣም የተጀመሩ ጥረቶችን ዕውን ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ በጤና ተቋማት ተደራሽነትና የሰው ኃይል በማፍራት በተሰጠው ትኩረት በተለይም በጤና ኤክስቴንሽን ለሌሎች አገራት ምሳሌ የሆነ ለውጥ ነው ብለዋል።
ሚኒስቴሩ 30 ዓመታት ያስቆጠረውን የጤና ፖሊሲ ዘመኑን በዋጀ አግባብ ማሻሻያ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሆነ አንስተዋል።
ፖሊሲው በተለይም በጤና ተቋማት አገልግሎት ተደራሽነት፣ ጥራት፣ በእናቶችና ህፃናት ጤና፣ ጤና መድን፣ በጽዱ ጤና ተቋማትና አካባቢ መፍጠር ላይ ትኩረት ማድረጉን ተናግረዋል።
የምክር ቤት አባላትም ጽዱ ሀገርና ጤናማ ማኅበረሰብ ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት ዳር ለማድረስ ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የምክር ቤት አባላት በክረምት ወቅት ቆይታቸው በእናቶችና ህፃናት ጤና፣ የዲጂታል ጤና አገልግሎት አሰጣጥን ጨምሮ በምልከታና በውይይት የሚያመጧቸው ሃሳቦች ለፖሊሲ ግብዓት እንደሚሆኑ ተገልጿል።
ዝግጅት ላይ በሚገኘው የጤና ፓሊሲ የማኅበረሰብ ጤና ኬላዎች ከመከላከል ባሻገር አክሞ ማዳን እንዲችሉ ፍኖተ-ካርታ መቀመጡን በውይይቱ ላይ ተነስቷል።