ቀጥታ፡

የደም እጥረት ችግር ለመፍታት ህብረተሰቡ ደም ልገሳን ባህል ማድረግ አለበት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦በክረምት ወቅት የሚገጥመውን የደም እጥረት ችግር ለመፍታት ህብረተሰቡ ደም ልገሳን ባህል ማድረግ እንዳለበት የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ። 

በክረምት ወቅት የሚገጥመውን የደም እጥረት ለመፍታት ህብረተሰቡ በበጎ ፍቃድ የሚሰጥ ደም ልገሳን ባህል ማድረግ እንዳለበት የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት አሳስቧል። 

አገልግሎቱ ከሰኔ 2016 እስከ መስከረም 2017 ባሉት የክረምት ወራት 120 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል። 

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው ለኢዜአ እንዳሉት የትምህርት ቤቶችን መዘጋት ተከትሎ በክረምት ወራት የደም ለጋሾች ቁጥር ይቀንሳል። 

ከቋሚ ደም መለገሻ ቦታዎች ይልቅ አብዛኛው የደም ልገሳ መርሃ-ግብር የሚካሄደው በተንቀሳቃሽ ቡድኖች በመሆኑ የዝናቡ ወቅት የደም ልገሳውን እንደሚያስተጓጉለው ነው የተናገሩት። 

ይህን ተከትሎ በክረምት ወራት ደም ለማሰባሰብ የዘመቻ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመው በተለይም የኢትዮጵያ ደም ለጋሽ ወጣቶች ማህበር አባላት በአደባባዮች ቅስቀሳ በማድረግ ደም ልገሳው እንዲጠናከር እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል። 

ደም መለገስ የአንድ ጊዜ ተግባር አይደለም ያሉት ዶክተር አሸናፊ ቋሚ ደም ለጋሾች ሲኖሩ ጥራት ያለውና ደህንነቱ የተጠበቀ ደም ለታካሚዎች ማድረስ እንደሚያስችል ተናግረዋል። 

ከሰኔ ጀምሮ እስከ መስከረም ባሉት የክረምት ወራት 120ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ቢታቀድም እስካሁን ያለው አፈፃፀም ዝቅተኛ በመሆኑ በቀሪዎቹ ጊዜያት የታቀደውን ያህል ደም ለመሰብሰብ ህብረተሰቡ ደም እንዲለግስ ጥሪ አቅርበዋል። 

ህብረተሰቡ በማንኛውም ሰዓት ልታልፍ የምትችልን ህይወት ደም በመለገስ እንዲታደግ ጥሪ አቅርበዋል። 

በአገሪቱ 50 የሚጠጉ የደም ባንኮች መኖራቸውን አንስተው በቅርቡ አራት ተጨማሪ ደም ባንኮች ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ ይታሰባል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም