የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ሀገር በቀል የአፈር ጥበቃ እውቀቶች እንዲሰፉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ሀገር በቀል የአፈር ጥበቃ እውቀቶች እንዲሰፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ  (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሠራተኞች ጋር በመሆን አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

በመርሃ-ግብሩም ከሐረር አካባቢ እና ከኮንሶ የመጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጫካ ፕሮጀክት ባከናወኑት የአገር በቀል የእርከን ሥራ ላይ ችግኝ የመትከል መርሃ-ግብር ተከናውኗል፡፡

በዚህም ከዚህ ቀደም የነበሩ የባህርዛፍ ተክሎችን በአገር በቀል ችግኞች የመተካት ሥራ ተከናውኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከዚህ ቀደም ከነበረው አካሄድ በተለየ መልኩ እንዲከናወን እየተሰራ ነው ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ ለአብነትም በጫካ ፕሮጀክት በሚከናወንበት አካባቢ የሚስተዋለውን የአፈር መሸርሸር ለመታደግ ከሐረርና ከኮንሶ በመጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች የእርከን ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል። 


 

ይህም በአካባቢው በአፈር መሸርሸር ምክንያት ከዚህ ቀደም ችግኝ ለመትከል አዳጋች በሆኑ ሥፍራዎች የአረንጓዴ ልማት ሥራ እንዲከናወን አስችሏል ነው ያሉት፡፡

አሁን ላይ የአገር በቀል እጽዋቶችን ጨምሮ እንደ አፕል ያሉ ፍራፍሬዎችን የማልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኮንሶና የሐረር አርሶ አደሮች የእርከን ሥራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቃቸውን ገልፀው፤ በሌሎችም የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ መሰል አገር በቀል እውቀቶች በአገር አቀፍ ደረጃ ሊስፋፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሀገር በቀል የአካባቢ ጥበቃ እውቀቶች ውብ አካባቢ መፍጠር እንደሚቻል ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ  ያሉንን  አቅሞች በአግባቡ መጠቀም አለብን ብለዋል፡፡  

በችግኝ ዝግጅት፣ በቦታ መረጣ፣ በእርከን ሥራና በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ በትኩረት በመሥራት የችግኞችን የጽድቀት መጠን ከፍ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ የደን ሽፋን በቀጣይ 30 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤  ይህም የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር ለጤና የሚኖረው ሚና የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በቀጣይም የተራቆቱ አካባቢዎችን በማልማት የተሻለች ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም