ሠራተኛው ህዝብን በታማኝነት በማገልገል ሰላም ፀንቶ እንዲቀጥል የድርሻውን ሊያበረክት ይገባል-የጎንደር ከተማ አስተዳደር

ጎንደር፤ሐምሌ 4/2016 (ኢዜአ)፦ የመንግስት ሠራተኛው በተመደበበት የሥራ መስክ ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል ሰላም  እንዲጸና  የድርሻውን ማበርከት እንዳለበት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ገለፀ።

"ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም'' በሚል መሪ ሃሳብ የከተማው የመንግስት ሠራተኞች የሰላም ኮንፍረንስ ዛሬ ተካሂዷል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ ከንቲባ የህዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት አማካሪ አቶ ቻላቸው ዳኘው እንደገለጹት፣ የመንግስት ሠራተኛው ለከተማው ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ እያደረገ ያለውን አስተዋጾ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።


 

የህዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በመንግስት የተጀመሩ ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ሠራተኛው በተመደበበት የሥራ መስክ ሃላፊነቱን በላቀ ሁኔታ መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።

የመንግስት የሰላም ጥረቶች ሊሳኩ የሚችሉት በህብረተሰቡ ግንባር ቀደም ተሳትፎ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይ የመንግስተ ሠራተኛው የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። 

የሰላም ኮንፍረንሱ የመንግስት ሠራተኛው በሰላም፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ላይ የጋራ ግንዛቤ ጨብጦ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል። 

የመድረኩ ተሳታፊ አቶ አጣናው መኩሪያው በሰጡት አስተያየት፤ የመንግስት ሠራተኛው ለህዝቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሰላም ወሳኝ ነው ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የከተማው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እያከናወናቸው ያሉ የሰላም ግንባታ ሥራዎች የሚደገፉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በተመደቡበት የሥራ መስክ የህዝብን እርካታ የሚያረጋግጥ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

"የሰላም እጦት የከተማዋን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ስለሚገድብ የመንግስት ሠራተኞች ለሰላም አጥብቀን ልንሰራ" ይገባል ያሉት ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ እንዳልክ መኮንን ናቸው። 

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚነሱ የህዝብ ቅሬታዎች የመንግስት ሠራተኛው የቅንነትና የታታሪነት መጓደል መገለጫ በመሆናቸው ህዝቡን የሚያረካ ተግባራት በመፈጸም ሃላፊነታቸውን በተሻለ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። 

በኮንፍረንሱ ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና የመንግስት ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን የአገሪቱንና የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ የዳሰሰ ሰነድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም