የገጠር መንገድ ተደራሽነትን ለማስፋት የ407 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦የገጠር መንገድ ተደራሽነትን ለማስፋት የ407 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ መሆኑን የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የቀጣይ የፕሮጀክት አተገባበርን አስመልክቶ ለብዙኃን መገናኛ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፤ መንግሥት ጥናትን መሠረት በማድረግ የዜጎችን የመሠረተ-ልማት ፍላጎት ተደራሽነት  ለማስፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

ከዚህ ቀደም  በገጠር  መንገድ ተደራሽነት በርካታ  መንገዶች  ተገንብተው ለሕዝብ አገልግሎት መዋላቸውን ተናግረዋል።

ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበር የ407 ሚሊየን ዶላር የገጠር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ አድርገዋል።

የፕሮጀክቱ ገንዘብ 300 ሚሊየን ዶላር  ከዓለም ባንክ በድጋፍ የተገኘ ሲሆን፤ 107 ሚሊየን  ዶላር ከክልል  መንግሥታት የተውጣጣ እንደሆነ  ተናግረዋል።  

ለፕሮጀክቱ የተመደበው ገንዘብ ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጀትን በሚያከፋፍልበት ቀመር  መሠረት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንደሚከፋፈል ገልፀዋል።  

ፕሮጀክቱ ድሬዳዋን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች በሚገኙ 126 ወረዳዎች የገጠር መንገዶችን          ከዋና ዋና መንገዶች ጋር በማስተሳሰር ዜጎችን የመንገድ መሠረተ-ልማት ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በዚህም 7 ሺህ 554 ኪሎ ሜትር መንገዶች ላይ አዳዲስና ማሻሻያ እንደሚደረግ፣ 10 ሺህ 71 መንገዶች ጥገና፣ 373 ተንጠልጣይ ድልድዮችና 715 ድልድዮች እንደሚገነቡ አስረድተዋል።  

በአገሪቱ የገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን የግብርና  ምርታቸውን ወደ ገበያ በማውጣት ለሸማቾቹ  እንዲያቀርቡ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።

የመንገድ መሠረተ-ልማት ፕሮጀክቱ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዓላማ ያደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ  በመልክዓ-ምድር አቀማመጥ ምክንያት የተነጠሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል  እንደሆነም  ተናግረዋል።  

ፕሮጀክቱ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አዳዲስ የመንገድ መሠረተ-ልማት ተደራሽነታቸውን እንዲያሰፉና መንገዶችን የመጠገን አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ድጋፍ እንዲያገኙ  የሚያደርግ እንደሆነም አብራርተዋል።   

ፕሮጀክቱ  በኮንስትራክሽን  ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ድጋፍ የሚደረግበትና በዘርፉ  ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነም አንስተዋል።

አርሶ አደሩ የሚያመርተው ምርት  በዲጂታል የግብይት ሥርዓት አማካኝነት ለሸማቹ ማኅበረሰብ እንዲደርስ  በፕሮጀክቱ እንደሚሰራም ተናግረዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም