የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ነሐሴ 5 ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በኢትዮጵያ ቡና መካከል ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ሁለቱ ክለቦች ዋንጫን ለማንሳት የሚጫወቱት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግና የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ መሆናቸውን ተከትሎ ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚከናወን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

ጨዋታው የሚደረግበት ሜዳ በቀጣይ ይፋ እንደሚደረግም ጠቁሟል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ ኢትዮጵያ ቡና የ2016 የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ናቸው።

በተያያዘ ዜና የተጫዋቾች የዝውውር ጊዜ የሚከፈትበት ቀን ላይ ማስተካከያ ማድረጉን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።

የ2017 የውድድር ዘመን የዝውውር ጊዜ ሐምሌ 15 ቀን 2016 እንደሚከፈት ይፋ ተደርጎ ነበር።

ይሁንና ቀኑን ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ምክንያት የዝውውር መስኮቱ ሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲከፈት መወሰኑን ነው ፌዴሬሽኑ ያስታወቀው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም