በክልሉ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስቻሉ ናቸው--አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደ

ሀዋሳ ፤ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስቻሉ መሆናቸውን የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደ ገለፁ።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 3ኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።


 

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ዋና አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ፋንታዬ፣ ምክር ቤቱ ለ2016 ያፀደቀው በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ ስለመዋሉ በተለያየ መንገድ ሲከታተልና ሲገመግም መቆየቱን ተናግረዋል።

በምክር ቤቱ ክትትልና ምልከታ መሠረት በክልሉ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በግብርናው ዘርፍ ከእንሰት ልማት ጀምሮ የህዝቡን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡ ውጤታማ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውንም ጠቅሰዋል።

በእንስሳት ልማት ዘርፍ በተለይ በዶሮ እና በወተት ላሞች የተሻሻሉ ዝርያዎችን በስፋት በማሰራጨት ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።

ወጣቱን በተመረጡና ውጤታማ በሚያደርጉ የግብርና ልማት ዘርፎች እንዲሰማራ የተሰራው ስራ ውጤት የተገኘበት መሆኑንም አፈጉባኤዋ አስረድተዋል።

የክልሉን ሠላምና ፀጥታ አጠናክሮ የማስቀጠል ስራው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራበት መቆየቱን  የገለጹት አፈ ጉባኤዋ፣ በእዚህም ህዝቡን ባለቤት ያደረጉ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በከተሞች ዘመናዊ የደህንነት ማስጠበቂያ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ የሠላምና ፀጥታ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ወይዘሮ ፋንቱ ገልጸው፣ ከህብረተሰቡ በተሰበሰበ አንድ ቢሊዮን ብር በሁሉም ወረዳዎች የፖሊስ ተቋማት መገንባታቸውንና ተቋማቱ በዘርፉ ለተገኘው ውጤት አስተዋጾ እንዳላቸው  ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም