በቀጣናው አስተማማኝ ሰላም የሰፈነው የፀጥታ ሀይሉና ህብረተሰቡ ተቀናጅተው በመስራታቸው ነው- ጄኔራል አበባው ታደሰ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦በቀጣናው አስተማማኝ ሰላም የሰፈነው የፀጥታ ሀይሉና ህብረተሰቡ ተቀናጅተው በመስራታቸው ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ።

በጄኔራል አበባው ታደሰ የተመራ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች የፀጥታ ሃይል አመራሮች የተገኙበት ቡድን በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የሚገኙ የግዳጅ ቀጣናዎችንና በአካባቢው የተሰማሩ የፀጥታ ሃይሎችን ተመልክቷል።


 

ጄኔራል አበባው ታደሰ በዚህ ጊዜ እንደተናገሩት በሶማሌ ክልል የሚነፍሰው የሰላም አየር ወደ ሌሎች ክልሎች ተንሰራፍቶ ሀገራችን ወደ ልማት የምትሸጋገርበት ጊዜ እሩቅ አይደለም።

በአጠቃላይ በሠራዊታችን ብርቱ ተጋድሎ ቀጣናው ሰላሙ የተረጋገጠው ምስራቅ ዕዝና የክልሉ ህዝብና ፖሊስ እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ በከፈሉት መስዋዕትነት በመሆኑ ሀገር ሁልጊዜም እንደምትኮራባቸው ተናግረዋል።

አልሸባብና የኢትዮጵያን እድገትና ብልፅግና የማይፈልጉ አካላት ተቀናጅተው በመስራት በርካታ ጊዜ የሽብር ተግባር ለመፈፀም ቢሞክሩም በሠራዊቱና በህዝቡ የነቃ ተሳትፎና ትግል ፍላጎታቸውን ማምከን ተችሏል ብለዋል።

ቀጣናው ሀገርን መለወጥ የሚችል ትልቅ ስራ የሚሰራበት እንደመሆኑ ሰራተኞች ደህንነታቸው ተጠብቆ ያለ ስጋት እንዲሰሩ በማስቻል የፀጥታ ሀይሉ ከመከላከያ ሰራዊታችን ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።

የፀጥታ ሀይሉ ጥምር ኮሚቴ ስራውን አጠናክሮ በመቀጠል ግዳጁ የተሳካ እንዲሆን ተልዕኮውን በሚገባ እየተወጣ ሲሆን በቀጣይም ህዝቡን እንደ አንድ ኮሚቴ በመጠቀም በልማት ስራው ተሳታፊ ማድረግ የጥምር ኮሚቴው አብይ ተግባር መሆን እንደሚገባው ማሳሰባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም