የኢትዮጵያ አምባሳደሮች በማይናወጥ የሀገር ፍቅርና ታማኝነት ሀገራችሁን ማገልገል አለባችሁ- አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ

አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች በማይናወጥ የሀገር ፍቅርና ታማኝነት ሀገራችሁን ማገልገል አለባችሁ ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ አሳሰቡ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ከዛሬ ጀምሮ ለ15 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሥልጠና መሥጠት ጀምሯል። 


 

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ፤ ለሀገር ፍቅር በመሰዋዕትነት ጭምር ዋጋ መክፈል እንደሚገባ አንስተዋል።

የዲፕሎማሲው መስክ ሀላፊነቱ ድርብርብ ነው ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ የወቅቱን የዲፕሎማሲ አውድ በፍጥነት በመረዳት ሀገርን በቅንነትና ታማኝነት ማገልገል ይገባል ብለዋል።

በተለያዩ ሀገራት የምትመደቡ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በማይናወጥ የሀገር ፍቅርና በፍፁም ታማኝነት ሀገራችሁን ማገልገል አለባችሁ ሲሉ አሳስበዋል።

አሁን ላይ በፍጥነት ተለዋዋጭ እየሆነ የመጣውን የጂኦፖለቲካዊ አሰላለፍ በአግባቡ በመረዳትና በመቃኘት መስራትም ይገባል ብለዋል።  

በመሆኑም አዲሱን የዲፕሎማሲ አሰላለፍ በቅጡ በመረዳት ሀገርና መንግስት የጣለባችሁን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ሁኑ ሲሉም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም