ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ በመድረሱ የእርሻ ስራችንን በአግባቡ እንድናከናውን አስችሎናል-አርሶ አደሮች 

ሰቆጣ ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ  በወቅቱ  በመድረሱ የመኽር እርሻ የዘር ስራቸውን በወቅቱ ለማከናወን እንዳስቻላቸው በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ። 

በብሔረሰብ አስተዳደሩ በክረምት መኸር እርሻ ከ55 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑም ተገልጿል። 

የሰቆጣ ወረዳ የ024 ፋያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በላይ እንግዳ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የስንዴ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በመጠቀም ሩብ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ችለዋል። 

በግብርና ባለሙያዎች በተሰጣቸው ምክረ ሃሳብ መሰረት ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመመካከር በኩታ ገጠም በጋራ መሸፈን እንደቻሉም ገልፀዋል። 

ለመኸር ሰብል ልማት ስራው ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ መድረስ በመቻሉ የዘር ስራቸውን በወቅቱ እንዲያከናውኑ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። 


 

አርሶ አደር ምሬ ካሴ በበኩላቸው፤ ግማሽ ሄክታር መሬት ማዳበሪያን በመጠቀም ስንዴን በኩታ ገጠም መሸፈን እንደቻሉ ገልፀዋል። 

የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በማግኘታቸው የመኸር ወቅት የሰብል ዘር ስራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንዳገዛቸው አመልክተዋል። 

በኩታ ገጠም ማልማት በመቻላቸው የአረምና የተባይ መከላከል ስራ በጋራ ለማከናወን እንደሚያስችላቸውም ጠቁመዋል። 

ቀደም ባሉት ጊዜያት በማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ምክንያት በወቅቱ የሰብል ዘር ስራ ለማከናወን ይቸገሩ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ዓለሙሽ እንግዳ ናቸው። 

በዘንድሮው ዓመት ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ በመቅረቡ ምክንያት በፍጥነት መዝራት መቻላቸውን አረጋግጠዋል።

የ024 ፋያ ቀበሌ የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ ደስታ ጉለሽ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው መኸር እርሻ በቀበሌው 117 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ስንዴ መሸፈን ተችሏል። 

አርሶ አደሩ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን በመጠቀም በመስመር የመዝራት ልምዱ እያደገ መምጣቱን ገልፀው፤ ምርታማነትን ለማሳደግ ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። 


 

በብሔረሰብ አስተዳደሩ በ2016/17 የምርት ዘመን 142 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን የተናገሩት ደግሞ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ ናቸው። 

እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም 55 ሺህ 681 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር መሸፈን የተቻለ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥም አንድ ሺህ ሄክታር መሬት በጤፍ፣ በማሽላና በስንዴ ሰብሎች በኩታ ገጠም የለማ ነው ብለዋል። 

ምርታማነትን ለማሳደግ 63 ሺህ 167 ኩንታል ማዳበሪያ ቀርቦ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ሲሆን፤ 1 ሺህ 36 ኩንታል የተለያዩ የሰብል ምርጥ ዘር መቅረቡን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም