የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዓለም አቀፍ አዝማሚያዎችን ታሳቢ በማድረግ ለሀገር ጥቅምና ለዜጎች አብሮነት መጎልበት በትኩረት ይሰራል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዓለም አቀፍ አዝማሚያዎችን ታሳቢ በማድረግ ለሀገር ጥቅምና ለዜጎች አብሮነት መጎልበት በትኩረት እንደሚሰራ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በተካሄደው የሚዲያ ለሀገር 2016 ልዩ ተሸላሚ ሆኗል።

ሽልማቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተቀብለዋል።


 

ዋና ስራ አስፈጻሚው ኢዜአ የተሰጠው ልዩ ዕውቅና የሀገርና ህዝብን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ ለብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ ክብር የበለጠ ለመስራት ተጨማሪ ጉልበት እንደሚሆን ገልጸዋል።

ዕውቅናው ሙሉ ስለሆንን ሳይሆን ነገ በበለጠ ትጋት ብሄራዊ ጥቅምን መሰረት በማድረግ እንድንሰራና ተልዕኮዎቻችንን በአግባቡ እንድንወጣ በማሰብ የተሰጠ ነው ብለዋል።

እስከ አሁን ከሰራነው ይልቅ ከዚህ በኋላ የሚጠብቀን እንደሚበልጥ በመገንዘብ በቀጣይ ለሀገርና ህዝብ ጥቅም በበለጠ እንድንሰራ የተሰጠ አደራ ጭምር ነው ብለዋል።

ለብሄራዊ ጥቅምና ለሀገር ክብር ቅድሚያ መስጠት ለራስ ክብርና ጥቅም ቅድሚያ መስጠት በመሆኑ በትኩረት ልንሰራበት ይገባል ነው ያሉት።

ድህነት ክብር የሌለው መሆኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያ ልትደርስበት የምትሻው ብልጽግና እንዲረጋገጥ በጋራ መትጋት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ዕውቅናው የኢዜአ ሰራተኞች የተቋማቸውን ብሔራዊ መግባባት የመፍጠር ተልዕኮ ታሳቢ በማድረግ ባከናወኑት ስራ የተገኘ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።


 

በቀጣይም ዓለም አቀፍ አዝማሚያዎችን ታሳቢ በማድረግ ለሀገር ጥቅምና ክብር እንዲሁም ለዜጎች አብሮነት መጎልበት በትኩረት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

ኢዜአ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ያለውን መስተጋብር በማጠናከር ትልልቅ አገራዊና ቀጣናዊ የይዘት ስራዎችን ተደራሽ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መገናኛ ብዙሃንን ለቀጣይ ስራ የበለጠ በሚያነሳሳ መልኩ ማበረታታቱ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ልዩ ትኩረት ሰጥተው የኢትዮጵያን ብልጽግና በማረጋገጥ ጉዞ ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጉልህ ሚና ያላቸው በመሆኑ ዕውቅና በመስጠታቸው አመስግነዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም