የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ጉባኤ መካሄድ ጀመረ

ሀዋሳ፣ሐምሌ 4/2016 (ኢዜአ)፡-የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 3ኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን በሀዋሳ ከተማ ማካሄድ ጀመረ።

የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ይወያያል ተብሎም ይጠበቃል።

ጉባኤው በዛሬው ውሎ የምክር ቤቱን የ2016 በጀት የአፈጻጸም ሪፖርትና የ2017 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ አድምጦ እንደሚያጸድቅ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት በማድረግ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የወጣው መርሀግብር እንደሚያሳየው በአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድና የማስፈጸሚያ በጀትም ቀርቦ በጉባኤው ውይይት ከተደረገበት በኋላ ይጸድቃል።

በተጨማሪም ጉባኤው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ኦዲት ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድና በጀት ላይ ውይይት ያደርጋል።

በጉባኤው የተለያዩ አዋጆችም ቀርበው የሚጸድቁ ሲሆን የዳኛ ሽኝትና ሹመትም እንደሚኖር ተመላክቷል።

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ አስፈጻሚ ተቋማት ዕውቅና እና ሽልማት እንደሚሰጥ የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም