አረንጓዴ አሻራ በፊት የተጎዳውን መሬት የታደገና አካባቢያችንን ወደ ለምለምነት የመለሰልን ነው -  የጎሮ ጉቱ ወረዳ አርሶ አደሮች 

ሐረር ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦  የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  በፊት የተጎዳውን መሬት የታደገና አካባቢያችንን ወደ ለምለምነት የመለሰልን ነው ሲሉ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የጎሮ ጉቱ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

"የምትተክል አገር የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ  የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጎሮ ጉቱ ወረዳ ቡርቃ ጃለላ ተራራ ላይ የተሳተፉት የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩት "በጋ እና ክረምት በመስራት አካባቢያችንን ወደ ለምነት፤ መሬቱንም ወደ ምርታማነት መልሰነዋል"።

በተራራው ላይ ችግኝ ሲተክሉ ያገኘናቸው በወረዳው የቡርቃ ኤላ ቀበሌ አርሶ አደር  ሙዘሚል ቃሴ  እንዳሉት "መጀመሪያ ባለማወቃችን ደን ጨፍጭፈናል፤ የአፈር መሸርሸርም አጋጥሟል፤ አካባቢያችንም ተራቁቶ ቆይቷል"።

የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በፊት የተጎዳውን መሬት ታድጎናል፤ ውጤቱንም ስላየን ሁሉም በወቅቱ የተፋሰስ ልማት ከመሥራት ባለፈ ችግኝ ተክሎ ይንከባከባል ብለዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት አካባቢያችንን ከድርቅ በመታደግ ወደ ለምለምነት ቀይሮልናል ብለዋል።


 

በየወቅቱ በአረንጓዴ አሻራ የምንተክላቸውን ችግኞች በአግባቡ እንከባከባለን ያሉት ደግሞ ሌላው አርሶ አደር  መብራቴ እንግዳ ናቸው።

በአካባቢያቸው በለሙ ተፋሰሶች  ውስጥ  ችግኝ መትከላቸው እና የተተከሉ እጽዋቶች በመጽደቃቸው ዝናብ በወቅቱ እንዲዘንብ፣ እርጥበታማ አየር እንዲኖር በማስቻሉ የግብርና ስራን በተሻለ መልኩ ለመከወን  እንዳስቻላቸው ነው የተናገሩት።


 

በወረዳቸው በበጋ ወቅት 15ሺህ ሄክታር መሬት በሚሸፍን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተለያዩ የእርከን ስራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ደግሞ የጎሮ ጉቱ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሚፍታህ መሐመድ ናቸው።

ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑት ስራዎች የአየር መዛባትና የአፈር መሸርሸር  ከመከላከል ባለፈ ለካርቦን ሽያጭ የሚያበቃና ምሳሌ የሚሆን ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።


 

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሐመድ እንዳሉት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች በዞኑ ጠፍቶ የነበረውን የከርሰ ምርድ ውሃን በመመለሱ  አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደረገና ተስፋ የሰጠ ነው።

በተለይም የአርሶ አደሩን  ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት ያስቻለና በመስኖ የበጋ ስንዴ ልማትን በማስፋት ተጠቃሚነቱን ያጎለበተ  መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ  ምክትል ሃላፊ አቶ ኤሊያስ ከዲር በበኩላቸው በክልሉ በለሙ ተፋሰሶች ላይ በሚከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  ችግኝ ተከላ ምርትና ምርታማነትን ለማጎልበት በሰብልና እንሰሳት ሃብት ልማት የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም በአረንጓዴ አሻራ የተሸፈኑ አካባቢዎችና ተፋሰሶች በከብት ማደለብ፣ በንብ ማነብና በፍራፍሬ ልማት የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ማስቻላቸውንና  ወጣቶችም በዘርፉ የስራ እድል እንዲያገኙ እድል መፍጠሩን አስተድተዋል።

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ደረጃ ትናንት በጎሮ ጉቱ ወረዳ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም