የ #አረንጓዴዓሻራ የችግኝ ተከላ ወቅት ሥራችን ያስቀመጥነውን ግብ በሚያሳካ መልካም አጀማመር ላይ ይገኛል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2016(ኢዜአ)፦ የ #አረንጓዴዓሻራ የችግኝ ተከላ ወቅት ሥራችን ያስቀመጥነውን ግብ በሚያሳካ መልካም አጀማመር ላይ ይገኛል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ በጫካ ፕሮጀክት ስፍራ የአፕል ችግኞችን ተክለናል ብለዋል።


 

የኅብረተሰባችንም የችግኝ ተከላ ተነሳሽነት ከፍተኛ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በአካባቢው የተደረገውን የዘንድሮውን ችግኝ ተከላ ለየት የሚያደርገው ቀድሞ የነበረው የባህርዛፍ ሽፋን ተወግዶ በሀገር በቀል የእርከን ሥራ እና ተክል የተተካ መሆኑ ነው ሲሉም አክለዋል።


 

ከሀረር አካባቢ እና ከኮንሶ የመጡ ህዝቦቻችን አፈር እንዳይሸረሸር የሚያደርገውን ጊዜ የማይሽረውን ክህሎታቸውን አካፍለውናል ብለዋል።


 

በከተሞች የምንሠራውን የአረንጓዴ አሻራ ጥረቶቻችንን በጋራ በማስፋፋት የአዲስ አበባን አረንጓዴ ሽፋን መጨመር እንችላለን ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም