እንግሊዝ በአውሮፓ ዋንጫው ኔዘርላንድን በማሸነፍ የፍጻሜ ተፋላሚ ሆነች

አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ሁለተኛ የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር እንግሊዝ ኔዘርላንድን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ አለፈች።

በሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ የ21 ዓመቱ የፓሪስ ሴይንት- ጀርሜን የአጥቂ አማካይ ዣቪ ሲመንስ በ7ኛው ደቂቃ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ የግል ብቃቱን ተጠቆሞ ያስቆጠራት ግብ ኔዘርላንድን መሪ አድርጋለች።

ይሁንና እንግሊዝ በ18ኛው ደቂቃ ያገኘችውን የፍጹም ቅጣት ምት የ30 ዓመቱ የብሔራዊ ቡድን አምበልና የባየር ሙኒክ አጥቂ ሀሪ ኬን ወደ ግብ በመቀየር ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ኬን በአውሮፓ ዋንጫ ከመረብ ላይ ያሳረፋቸውን ግቦች ወደ 3 በማድረስ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፋክክር ላይ ግለት ጨምሯል።

በተጨማሪም አጥቂው በአውሮፓ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች 6 ጎሎች ያስቆጠረ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል።

ተቀይሮ የገባው የ28 ዓመቱ የአስቶንቪላ አጥቂ ኦሊ ዋትኪንስ በ91ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ እንግሊዝን በባከኑ ደቂቃዎች አሸናፊ አድርጓል።

እንግሊዝ በጨዋታው የኳስ ቁጥጥርና ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በማደግ ከተጋጣሚዋ የተሻለች ነበረች።

በአንጻሩ ኔዘርላንድ በመልሶ ማጥቃት የጨዋታ ስልትን ይዞ ቀርቧል።

ውጤቱን ተከትሎ እንግሊዝ ለፍጻሜው ደርሳለች። ከስፔን ጋር ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም 74 ሺህ 745 ተመልካች በሚያስተናግደው የበርሊን ኦሊምፒክ ስታዲየም ዋንጫውን ለማንሳት ትፋለማለች።

ኔዘርላንድ የደረጃ ጨዋታ ባለመኖሩ ምክንያት በጀርመን የነበራት ቆይታ ዛሬ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም