ቀጥታ፡

የተሰጠን ዕውቅና ለብሔራዊ  ጥቅም መከበርና ለዜጎች አብሮነት መጎልበት እንድንሰራ ተጨማሪ ኃላፊነት የወሰድንበት ነው - የመገናኛ ብዙኃን አመራሮች

 አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ የተሰጠን ዕውቅና ለብሔራዊ ጥቅም መከበርና ለዜጎች አብሮነት መጎልበት እንድንሰራ ተጨማሪ ኃላፊነት የወሰድንበት ነው ሲሉ የመገናኛ ብዙኃን አመራሮች ገለጹ፡፡

"ሚዲያ ለሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ የመገናኛ ብዙሃን እውቅና መርሃ ግብር በአድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር ላከናወኗቸው ተግባራት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እውቅና ተሰጥቷል፡፡

በመርሃ ግብሩም በዝርዝር መስፈርቶች ተመዝነው የተለዩ 11 የህዝብ እና የንግድ መገናኛ ብዙሃን እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ደግሞ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

እውቅና የተሰጣቸው መገናኛ ብዙኃን አመራሮች፤ እውቅናው የበለጠ እንዲሰሩ መነሳሳትን እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡


 

የኢዜአ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፤  ኢዜአ የተሰጠው ልዩ ዕውቅና የሀገርና ህዝብን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ ለብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ ክብር የበለጠ ስራ ለመስራት ተጨማሪ ጉልበት እንደሚሆን ገልጸዋል።

ዕውቅናውም የኢዜአ ሰራተኞች ተቋማቸው የሰነቀውን ብሔራዊ መግባባት የመፍጠር ራዕይ ታሳቢ በማድረግ ባከናወኑት ስራ የተገኘ ውጤት ነው ብለዋል።

በቀጣይም ዓለም አቀፍ አዝማሚያዎችን ታሳቢ በማድረግ ለሀገር ጥቅምና ክብር እንዲሁም ለዜጎች አብሮነት መጎልበት በትኩረት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።


 

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ዋና ስራ አስፈፃሚ ጌትነት ታደሠ በበኩላቸው፤ ዕውቅናው ለሀገር ዕድገት፣ ብሔራዊ መግባባት እንዲሁም ሀገራዊ ክብር ተጨማሪ ኃላፊነት የወሰድንበት ነው ብለዋል።

ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም ኅብረብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ የይዘት ስራዎች ላይ በትኩረት ለመስራት ከፍተኛ ተነሳሽነትን የሚፈጥር መሆኑንም እንዲሁ፡፡


 

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አድማሱ ዳምጠው፤ የመገናኛ ብዙኃን ስራ የትብብር ስራ በመሆኑ ዕውቅናው የጋዜጠኞች በዕውቀት ላይ የተመሰረተ መረጃን ለህዝብ እንዲያደርሱ ተነሳሽነትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ሀገርና ትውልድን በመገንባት ሂደት ሙያዊ ነፃነትን ከስራ ኃላፊነት ጋር በማጣጣም እውነተኛ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።


 

የኢቢ ኤስ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስፈፃሚ አማን ፍስሃጺዮን ኢንዳስትሪውን በመቀላቀል ላይ የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት  ለሀገር ልማትና ህዝቦች አብሮነት መጎልበት እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በቀጣይም በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ የተሻለ ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲፈጠር በትኩረት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።


 

የኦሮሚያ ብሮድካትንግ ኔትወርክ (ኦ ቢ ኤን) ስራ አስፈፃሚ ግዛቸው ጋቢሳ፤ ዕውቅናው መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛ መረጃን ለህዝብ በማድረስ ለሀገር ዕድገት በትጋት እንዲሰሩ ድርብ ኃላፊነትን የሰጠ መሆኑን አንስተዋል።


 

በተመሳሳይም የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ፤  ዕውቅናው ተቋማቸው ለቀጣይ ስራ ስኬት እያከናወናቸው ለሚገኙ የማሻሻያ እርምጃዎች ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በቀጣይም በመዲናዋ እየተከናወኑ የሚገኙ ስኬታማ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የልማት ስራዎችን ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም