በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሰው ኃይል የማብቃትና የመደገፉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል -ሚኒስቴሩ 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሰው ኃይል የማብቃትና የመደገፉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት ከቦይንግ እና ፋሴሳ ከተሰኙ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በስፔስ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ያሰለጠናቸውን ከ120 በላይ ተማሪዎች አስመርቋል።

ተመራቂዎቹ በስልጠና ቆይታቸው አነስተኛ መጠን ያለው ሳተላይት (ኪውብሳት) ጽንጸሀብ፣ ሳተላይቶች ሲመጥቁ የሚቆዩበት ከባቢ ያለው ግፊት፣ መጠነ ሙቀት እና የጨረር ሁኔታን ተገንዝበው ለዚህ የሚስማማ ሳተላይት ግንባታ ላይ ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉ ተገልጿል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዲጂታል ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በስፔስ ዘርፉ ግንዛቤያቸው የላቁ ወጣቶችና ታዳጊዎችን ማፍራት ይገባል።

በሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዲሁም በስፔስ ሳይንስ ዙሪያ ወጣቶች አዳዲስ እውቀቶችን መገብየት አለባቸው ያሉት ሚኒስትር ደኤታው መሰል ስልጠናዎች ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል።   

በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ የሰው ኃይል ለማብቃት መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም መሰል ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።   

ቦይንግ ኩባንያን ጨምሮ በመስኩ ላይ ከሚሰሩ ድርጅቶችና ተቋማት ጋርም መንግሥት በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።    


 

የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ በበኩላቸው በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ባለሙያዎችን ለማፍራት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመቀናጀት በአስትሮኖሚ፣ ስፔስ ሳይንስ፣ ሪሞት ሴንሲንግን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።  

በሦስተኛ ዲግሪ ከ20 በላይ እንዲሁም በሁለተኛ ዲግሪ ከ35 በላይ ባለሙያዎች ተመርቀው ወደ ሥራ ዓለም መቀላቀላቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።   

በተመሳሳይም ኢኒስቲትዩቱ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በኤሮኔቲክ እንጂነሪንግና በኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ በድህረ ምረቃ ባለሙያዎችን እያፈራ መሆኑን ተናግረዋል።   

በስፔስ ዘርፍ ተሰጥኦ እና ፍላጎት ያላቸውን ታዳጊዎች ክህሎት ለማሳደግ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ የልጆች ስፔስ ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል መቋቋሙን ገልጸው በማዕከሉ በርካታ ተማሪዎች ግንዛቤና እውቀታቸውን እንዲያሳድጉ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።   

በዚህም ለአገሪቷ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ፕሮጀክቶችን መንደፍና የሙከራ ምርት ማምረት የቻሉ ተማሪዎችን መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት።  

  
 

የቦይንግ ኩባንያ የአፍሪካ ዳይሬክተር አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ እንዳሉት፤ ቦይንግ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ስፔስ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ራይዕ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።   

ቦይንግ ኩባንያ ወጣቱ ትውልድ በስፔስ ኢንዱስትሪው የጎላ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚያደርግውን  ድጋፍ እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።  


 

ከተመራቂዎች መካከል ተማሪ ቃልኪዳን ስጦታው በስፔስ ኢንዱስትሪው ለኢትዮጵያ የምችለውን ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ብላለች።   

ሌላው ተመራቂ ደግማዊ ዳዊት በበኩሉ ስልጠናው በእውቀትና ክህሎት አቅማችንን የበለጠ እንድናጎለብት ዕድል ፈጥሮልናል ብሏል።

 

 

 

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም