ታላላቅ የኢትዮጵያ ሚዲያዎችን መፍጠር የሚቻለው በቅድሚያ ብሔራዊ ጥቅሟ የተከበረ ጠንካራ ሀገር በመገንባት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ ታላላቅ የኢትዮጵያ ሚዲያዎችን መፍጠር የሚቻለው በቅድሚያ ብሔራዊ ጥቅሟ የተከበረ ጠንካራ ሀገር በመገንባት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

"ሚዲያ ለሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ የመገናኛ ብዙሃን እውቅና መርሃ ግብር በአድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል፡፡


 

በዚህም በኢትዮጵያ የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር ላከናወኗቸው ተግባራት እውቅና ተሰጥቷል፡፡

በመርሃ ግብሩም በዝርዝር መስፈርቶች ተመዝነው የተለዩ 11 የህዝብና የንግድ መገናኛ ብዙሃን እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ደግሞ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ ከቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ተያይዞ አሁን ላይ በርካታ መረጃዎች ለህዝብ ተደራሽ እንደሚደረጉ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በሀገር ብሔራዊ ጥቅም እና የህዝብ አብሮነት ላይ አደጋ የሚያስከትሉ መረጃዎች ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመምጣቱ አብራርተዋል፡፡ 

እነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች የኢትዮጵያ እዳ እንዳይሆኑ መገናኛ ብዙሃን በጥንቃቄ መስራት እንዳለባቸውም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ላይ እያጋጠሟት ያሉ ችግሮች የትናንት ስራ ውጤቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ለመጪው ትውልድ የተሻለ ሀገርን ለማሻገር ዛሬ ላይ በጥንቃቄ መስራት አለብን ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስቀደም እውነትን ለህዝብ ማድረስና ማሳወቅ እንዳለባቸውም ነው ያነሱት፡፡

የመረጃ ምንጮች የመገናኛ ብዙሃን መረጃ እውነትነት ላይ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ የመረጃ ምንጫቸውን ከውጭ ያደረጉ በርካታ ሀሰተኛ መረጃዎች እንደሚሰራጩ ጠቁመዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋጋጥ በሚከናወኑ ስራዎች ላይ የራሱ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለውም ነው ያወሱት፡፡

በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን በተለይ ለዘገባ የሚጠቀሙባቸውን የመረጃ ግብዓቶች ከየት እንደሆኑ በጥንቃቄ መመርመር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡   

መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን እውነት በማሳወቅ ረገድ አሁንም ብዙ እንደሚጠበቅባቸው ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት፡፡

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ በርካታ ሊወጡና ሊገለጡ የሚገባቸው እሴቶች እንዳሏት አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጠንካራ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እንደሚያስፈልጋት አንስተው፤ ነገር ግን ታላላቅ ሚዲያዎችን መፍጠር የሚቻለው በቅድሚያ ብሔራዊ ጥቅሟ የተከበረ ጠንካራ ሀገር በመገንባት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃን ለሚሰሯቸው ተግባራት እውቅና መሰጠቱ በጎ ጅምር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም