መገናኛ ብዙኃን የወል ትርክትን መሰረት ባደረገ መልኩ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙኃን የወል ትርክትን መሰረት  ባደረገ መልኩ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር  ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር )ገለጹ፡፡

"ሚዲያ ለሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ የመገናኛ ብዙሃን እውቅና መርሃ ግብር በአደዋ መታሰቢያ ተካሂዷል፡፡


 

በዚህም በኢትዮጵያ የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር ላከናወኗቸው ተግባራት እውቅና ተሰጥቷል፡፡

በመርሃ ግብሩም በዝርዝር መስፈርቶች ተመዝነው የተለዩ 11 የህዝብና የንግድ መገናኛ ብዙሃን እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ደግሞ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ ዶ/ር በዚሁ ወቅት፤ የመድረኩ ዓላማ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ለብሔራዊ ጥቅም መከበር እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ እውቅና መስጠት መሆኑን ገልጸዋል።

መገናኛ ብዙሀን ፖሊሲዎችን በመመርመር ብልሹ አሰራሮችን በማጋለጥ እና ፍትህ እንዲሰፍን እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ስርአት እንዲጎለብት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ለዜጎች ደህንነት፣ክብር፣ዘላቂ ልማት እንዲሁም ለኢኮኖሚ ብልጽግና መረጋገጥ አይነተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም እንዲሁ፡፡

ከዚህ አኳያ ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት የተዘጉ ሚዲያዎች እንዲከፈቱ መደረጉን ተናግረዋል።

አሳሪ ህግችን በማሻሻል የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አንስተው፤ ይህም መንግስት ዘርፉን ለማስፋፋት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡

ለእውቅና የበቁ መገናኛ ብዙሀንም በተቀመጡ ዝርዝር መስፈርቶች ተመዝነው  ከ50 ነጥብ በላይ ያስመዘገቡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

መገናኛ ብዙኃን የወል ትርክትን መሰረት  ባደረገ መልኩ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ያላቸውን ሚና አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።


 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው መንግስት በሪፎርም ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ሚድያ መሆኑን ገልጸዋል።

ሪፎርሙን ተከትሎ በርካታ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸው፤ ለአብነትም በርካታ የህግ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

ባልተለመደ መልኩ ከዚህ ቀደም ስድስት የነበሩ የዘርፉ የሙያ ማህበራት 44 መድረሳቸውን ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙሀን በአይነት በቁጥር እንዲሁም በቋንቋ እድገት ማሳየቱን ገልጸው በአጠቃላይ አሁን ላይ 272 መገናኛ ብዙሀን ፈቃድ ወስደው እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

በአሁኑ ሰአት 103 የቴሌቭዥን ጣቢያዎች መኖራቸውና ይህም ከለውጡ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር 312 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ለአብነት አንስተዋል፡፡

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም