በ2017 በጀት አመት ለመድኃኒት አቅርቦት 11 ቢሊየን ብር ተመድቧል - ኢዜአ አማርኛ
በ2017 በጀት አመት ለመድኃኒት አቅርቦት 11 ቢሊየን ብር ተመድቧል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦በ2017 በጀት አመት ለመድኃኒት አቅርቦት 11 ቢሊየን ብር በላይ መመደቡን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስቴር፣ ጤና ሚኒስቴር፣ የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና የትምህርት ሚኒስቴር የምክር ቤት አባላት ከህዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ ለምክር ቤቱ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት ከ11 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ አባወራዎችና ከ 55 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች በጤና መድህን ሽፋን መካተታቸውን አስረድተዋል።
በጤና መድህንና በሌሎች የህክምና አገልግሎቶች ላይ የሚነሳውን የመድኃኒቶች እጥረት ችግር ለመፍታት ባለፈው አመት 7 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ተመድቦ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።
የጤና መድህን አገልግሎትን ጨምሮ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እየሰፋ በመሄዱ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እየገጠመ መሆኑን ጠቁመው በ2017 በጀት አመት ለመድኃኒት አቅርቦት 11 ቢሊየን ብር በላይ መመደቡን ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈ በዘርፉ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በዲጂታላይዜሽን የታገዘ እንዲሁም ልዩ ኦዲቶችን በማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
የእናቶችና ህፃናት ሞትን ለመቀነስ መከላከል ላይ ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ ህክምናን ተደራሽ ለማድረግ፣ የጤና ተቋማትን ቅብብሎሽ የማዘመንና አምቡላንሶችን የማከፋፈል ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።
ተጀምረው ያልተጠናቀቁና ተጠናቀው ስራ ያልጀመሩ የጤና ተቋማት ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እንዲጠናቀቁ ይሰራልም ነው ያሉት።
እንደ ኮሌራ፣ ወባና ኩፍኝ ያሉ በሽታዎች ላይ እንደ አገር የተጀመረው የስምንት ሳምንት ንቅናቄ ስድስተኛ ሳምንቱ ላይ መድረሱንና በእነዚህ ጊዜያት ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለአብነትም በንቅናቄው ከተያዙ 52 ወረዳዎች ውስጥ አሁን ላይ በ40 ወረዳዎች ምንም አይነት የኮሌራ ሪፖርት አለመቅረቡን አንስተዋል።
የወባን በሽታ ለመከላከል ከ 500 ሺህ በላይ ቤቶች ላይ ርጭት መካሄዱንና ከ20 ሚሊዮን በላይ አጎበር ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ስርጭት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል ።
የአገር ውስጥ የህክምና ግብዓት ምርትን ከ 8 በመቶ ወደ 36 በመቶ ማድረስ መቻሉን አንስተው ይህም በመድኃኒትና ላቦራቶሪ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ አግዟል ብለዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ በህብረተሰቡ የተነሱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስተማማኝነትና ተደራሽነት ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡